የባህርዳር ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ግቢውን ለቀው ወጡ
(ኢሳት ዜና ሰኔ 7 ቀን 2010 ዓ/ም) ወኪላችን እንደዘገበው የሁለተኛ፣ የሶስተኛ እና በከፊል የአራተኛ ዓመት ተማሪዎች ከባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ኢንጂነሪንግ ፋክሉቲ ግቢ ለቀው ወጥተዋል።
ሰሞኑን የተፈጠረውን አለመግባባት ሁሪያ በትላንትናው ዕለት ከዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ፍሬው ጋር የተደረገው ውይይት ያለ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ፣ የዩኒቨርስቲው አመራሮች ተማሪዎች ግቢውን እንዲለቁ በማስታወቂያ አዘዋል፡፡ማስታወቂያውን ተከትሎ ተማሪዎች ግቢውን በመልቀቅ ወደ ቤተሰቦቻቸው ለመሄድ መገደዳቸውን ለማዎቅ ተችሏል፡፡
አንዳንድ ተማሪዎች ወደ አካባቢያቸው ለመሄድ ገንዘብ በማጣታቸው ሳቢያ፣ በከተማው ውስጥ በሚያውቋቸው ሰዎች ቤት በመጠለል ገንዘብ እስኪላክላቸው በመጠባባቅ ላይ ናቸው።
ተማሪዎቹ የሆሊስቲክ የፈተና አሰጣጥ ስርዓት እንዲቀየር ጥያቄ ሲያቀርቡ ቆይተዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በባህርዳር የፈለገ ህይወት ሆስፒታል የጤና ባለሙያዎች ለ2 ሰዓታት ያክል የስራ ማቆም አድማ አድርገዋል። ሰራተኞቹ የተለያዩ የመብትና የስራ ሁኔታ ጥያቄዎችን አቅርበዋል።
በአሁኑ ሰዓት በሆስፒታሉ ውስጥ ይሸጥ የነበረው መድሃኒት በማለቁ ህዝቡ ከውጭ መድሃኒት ለመግዛት በመገደዱ ምሬቱን በሰራተኞች ላይ መግለጹ ለአድማው አንድ ምክንያት ሆኗል። በውጭ የሚሸጡ መድሃኒቶች በሆስፒታሉ ከሚሸጡ መድሃኒቶች 500 ፐርሰንት ብልጫ ያላቸው በመሆኑ ህዝቡ ለከፍተኛ ምሬት ተደርጓል። በሆስፒታሉ መድሃኒት ቤት በ5 ብር ይሸጥ የነበረ መድሃኒት በግል መድሃኒት ቤቶች እስከ 120 ብር እንደሚሸጥ የጤና ባለሙያዎች ይናገራሉ።
በሆስፒታሉ ውስጥ ያለው የቀዶ ህክምና ክፍል ከፍ ያለ የጽዳት ችግር ስላለበት፣ ቀዶ ጥገና የሚደረግላቸው ህመምተኞች ለአንፌክሽን መዳረጋቸውንና የሟቾቹም ቁጥር መጨመሩን ሰራተኞች ይናገራሉ። በመጋቢት ወር ውስጥ ብቻ በዚሁ ክፍል ውስጥ ከቀዶ ጥገና በሁዋላ በኢንፌክሽን 27 ሰዎች መሞታቸውን፣ ይህም አሃዝ በአማካኝ መሞት ከነበረባቸው 5 ሰዎች በእጅጉ ከአምስት እጥፍ በላይ በልጦ እንደሚገኝ ባለሙያዎች ተናግረዋል።
ባለሙያዎች ለትርፍ ሰዓት ስራ የሚከፈላቸውን ገንዘብም በጊዜው ማግኘት አለመቻላቸውን፣ ሆስፒታሉ በየቀኑ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እያስገባ 50 ሚሊዮን የመድሃኒት እዳ አለመክፈሉንና በገንዘብ ችግር ላይ ነው መባሉ እንቆቅልሽ እንደሆነባቸውም ገልጸዋል።
ሆስፒታሉ ከፍተኛ ሙስና የሚካሄድበት ተቋም መሆኑን የሚናገሩት ባለሙያዎች፣ የክልሉ መንግስት ችግሩን በአፋጣኝ እንዲፈጣ ጠይቀዋል።