በገንዳ ውሃ ከተማ በተከሰተ የአሳት አደጋ 50 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ወደመ፡፡
(ኢሳት ዜና ግንቦት 29 ቀን 2010 ዓ/ም) በመተማ ወረዳ ገንዳ ውሃ ከተማ ከሚገኙ ፋብሪካዎች መካከል የህወሃት ሰዎች ንብረት እንደሆነ በሚነገርለት” ካልሚ የሰሊጥ ፋብሪካ” ላይ ሰሞኑን በተከሰተው ከፍተኛ የአሳት አደጋ በሚሊዮን የሚገመት ንብረት ወድሟል፡፡
ፋብሪካውን በበላይነት የሚመሩት አቶ ፍስሃ ጽዬን መሐሪ እንደተናገሩት ከ30 ሽህ ኩንታል በላይ ጥጥና ከ10 ሽህ ኩንታል በላይ ሰሊጥ ተከማችቶ የሚገኝበት መጋዝን ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት ላይ ባልታወቁ ሃይሎች በተነሳው እሳት ሙሉ በሙሉ ወድሟል፡፡
እንደ አቶ ፍስሃ ጽዬን ገለጻ አደጋውን ለመከላከል ጥረት ቢደረግም የእሳት አደጋ መኪና በአቅራቢያ ባለመገኘቱ ሁኔታውን ከባድ እንዳደረገው ተናግረዋል፡፡በከተማዋ የነበረው የወቅቱ ሙቀትም ለአሳት አደጋው መባባስ እንደምክንያት የሚጠቅሱት ባለሃብቱ የእሳት አደጋ መኪና ከጎንደር ከተማ እስኪመጣ ድረስ በፋብሪካው ንብረቶች ላይ ከፍተኛ ውድመት ደርሷል፡፡
ፋብሪካው 34 ቋሚ ሠራተኞች ቢኖሩትም አብዛኛው ተቀጣሪዎች የአካባቢው ወጣቶች ሳይሆኑ በዘመድ አዝማድ የተሰባሰቡ የክልል አንድ ሰዎች መሆናቸው፤ በአካባቢው ስራአጥ ወጣቶችና የከተማዋ ነዋሪዎች ላይ ቅሬታ ማሳደሩን አስተያዬት ሰጪዎች ይናገራሉ፡፡