ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 29/2010) የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት በነበሩት በአቶ ኢሳያስ ባህረ እንዲሁም በምክትላቸውና በሌሎቹ የባንኩ ሃላፊዎች ላይ የፌደራል ፖሊስ የሌብነት ምርመራ ጀመረ።
በአጠቃላይ 30 የሚሆኑ ግለሰቦችን በተመለከተ በሐገሪቱ የሚገኙ ባንኮች ሪፖርት እንዲያቀርቡ መጠየቃቸው ታውቋል።
ተጠርጣሪዎቹ በሌብነትና በዘረፋ የሚፈለጉ መሆናቸውም ተመልክቷል።
ከጋምቤላ የእርሻ ፕሮጀክቶች ጋር በተያያዘ በ5 ቢሊየን ብር ብክነትና ሌብነት ሲወጀነሉ የነበሩት የሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ አባልና የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ባህረ ከስልጣን የተነሱት ከአመት ከመንፈቅ በፊት ነበር።
በጋምቤላ እርሻ ለተሰማሩ በአብዛኛው የሕወሃት አባላት ለሆኑት ግለሰቦች በብድር የተሰጠው ገንዘብ በአብዛኛው በተባለው የእርሻ ልማት ላይ አለመዋሉ የተጋለጠው በመንግስት የተዋቀረ ኮሚቴ ባደረገው ምርመራ ነው።
ተበዳሪዎቹም ገንዘቡን ሳይመልሱ ተጨማሪ ገንዘብ ሲወስዱ መቆየታቸው ተመልክቷል።
ጥቂት የሚባሉት ገንዘቡን ከወሰዱ በኋላ ከሀገር ሲጠፋ ሌሎቹ ደግሞ ያለመያዣ የተሰጣቸውን ገንዘብ በአዲስ አበባና በመቀሌ ሕንጻ እንደገነቡበት ተገልጿል።
በግብርናው ዘርፍ ተሰማራን ብለው የግብርና መሳሪያ የሌላቸው ግለሰቦች መኖራቸውም በወቅቱ ይፋ ሆኗል።
በአጠቃላይ 5 ቢሊየን ያህል የሃገር ሃብት የባከነበትን ይህንን የዘረፋ ርምጃ ተከትሎ የልማት ባንኩ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ባህረ ከስልጣን እንዲነሱ ተደርገዋል።
ሆኖም በሌብነት ይጠየቃሉ ተብሎ ሲጠበቅ ያለከልካይ ከሃገር መውጣታቸው ተመልክቷል።
ባለስልጣኑ ከሃገር ከወጡ ከአንድ አመት በኋላ ወደ ስልጣን የመጣው የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አስተዳደር በአቶ ኢሳያስ ባህረ እንዲሁም የሳቸው ምክትል በነበሩት በአቶ ታደሰ ሀቲያና በሌሎች አራት የባንኩ ሃላፊዎች ላይ የሌብነት ምርመራ መጀመሩን አዲስ ፎርቹን ዘግቧል።
እንደ ጋዜጣው ዘገባ ከሆነ በአጠቃላይ የሌብነት ምርመራ የተጀመረባቸው 30 ያህል ሰዎች ናቸው።
እነዚህ ስማቸው የተጠቀሰና ያልተጠቀሰ 30 ያህል ሰዎች በሃገሪቱ ባንኮች ውስጥ ያላቸው የሒሳብ ሪፖርት ለፌደራል ፖሊስ እንዲቀርብ ትዕዛዝ ተላልፏል።