መንግስት የአልጀርሱን ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተቀብሎ ወደ ተግባር ለመለወጥ ዝግጁ መሆኑን ገለጸ
(ኢሳት ዜና ግንቦት 28 ቀን 2010 ዓ/ም) የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ለአለፉት 20 አመታት ሲከተለው የነበረውን ፖሊሲ በመቀየር ከኤርትራ መንግስት ጋር ወዳጅነት ለመመስረት ሲባል፣ “ መንግስት የአልጀርሱን ስምምነት እና የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ሙሉ ለሙሉ ተቀብሎ ተግባራዊ ለማድረግ የወሰነና ለተግባራዊነቱ ያለማመንታት በቁርጠኝነት የሚሰራ መሆኑን “ ዛሬ በዋወጣው መግለጫ አስታውቋል።
“እኔ እበልጥ፣ እኔ እበልጥ የሚል ፉክክር ለሁለቱም ህዝቦች የሚፈይደው ነገር አይኖርም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ለአፍሪካ ቀንድ ሀገሮችና አካባቢ የፖለቲካ ቀውስ መብረድና መረጋጋት ዘላቂው መፍትሔ የኢትዮጵያና የኤርትራ ጤናማ ግንኙነት መመሥረት ነው፡፡ይህን ባለማድረጋችን በርካታ ለሁለቱ እህትማማች ሀገሮችም ሆነ ለአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ትልቅ ፋይዳ ያላቸዉ እድሎች አምልጠዉናል፡፡ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ህዝቦች ቀድሞም ቢሆን ወዳጅ ነን፡፡ በደም፣ በባህል፣ በቋንቋ እና በረጅም ጊዜ የጋራ ታሪክ የተሳሰርን ሕዝቦች ነን፡፡” ያለው መግለጫው፣ የኤርትራ መንግስትም ተመሳሳይ አቋም በመውሰድ ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ የሰላም ጥሪያችንን ተቀብሎ በሁለቱም ወንድማማች ህዝቦች መካከል ከዚህ በፊት የነበረውን አብሮነትና ሰላም ወደነበረበት ለመመለስና በቀጣይም ዘላቂነቱን ለመጠበቅ ለተግባራዊነቱ ያለማመንታት በቁርጠኝነት እንዲሰራ እንጠይቃለን” ብሎአል።
በሌላ በኩል ደግሞ “ በመንግስት ይዞታ ሥር ያሉ በማምረት ወይም አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙትም ሆነ በግንባታ ላይ የሚገኙ የባቡር፣ የስኳር ልማት፣ የኢንዱስትሪ ፓርክ፣ የሆቴል እና የተለያዩ የማኑፋክቸሪንግ ድርጅቶች ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል በአክሲዮን ሽያጭ ወደ ግል ዘርፍ እንዲተላለፉ፣ እንዲሁም የኢትዮ ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች እና የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ድርጅት ትልቁን የአክስዮን ድርሻ መንግስት ይዞ ቀሪው አክሲዮን ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ባለሃብቶች እንዲተላለፍ፣ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡” ማስቀመጡንም መግለጫው አትቷል።