የቀድሞው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከፍተኛ የማኔጅመን አባላት የሙስና ወንጀል ምርመራ እየተደረገባቸው ነው።
(ኢሳት ዜና ግንቦት 28 ቀን 2010 ዓ/ም) እንደ ፎርቹን ዘገባ፣ በፌዴራል ፖሊስ የሙስና ወንጀሎች ጉዳይ ክፍል፣ ተጠርጣሪዎቹ በስማቸው ያስቀመጡት ገንዘብ ካለ መጠኑ እንዲገለጽለት ለሁሉም የንግድ ባንኮች ደብዳቤ ጽፏል።
ፖሊስ-ለንግድ ባንኮቹ በጻፈው በዚህ ደብዳቤ ላይ ስድስት የቀድሞ የልማት ባንክ አመራሮችን ጨምሮ የ30 ሰዎች ሰፍሯል።
ቀደም ሲል ባንኩን በፕሬዚዳንትነት ለረዥም ጊዜ ያገለገሉት አቶ ኢሳያስ ባህሬ እና በባንኩ የብድር አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ታደሰ ሀቲያ ፣ፖሊስ ትኩረት ካደረገባቸውና በደብዳቤው ካሰፈራቸው የቀድሞ የልማት ባንኩ ከፍተኛ አመራሮች መካከል ናቸው።
ይህ የፖሊስ ደብዳቤ ለንግድ ባንኮቹ የተላከው፣ አቶ ኢሳያስ ከሥልጣናቸው ከተሻሩ ከሁለት ዓመት፣ እንዲሁም አቶ ታደሰ ቦታቸውን ከለቀቁ ከአንድ ዓመት በኋላ ነው።
አቶ ኢሳያስ ከሥልጣናቸው የተሻሩት የዛሬ ሁለት ዓመት-የሕዝብ ፋይናንሺያል ኢንተርፕራይዝ ኤጄንሲ ዳይሬክተር ጄነራል ከሆኑት ከዶክተር ስንታዬሁ ወልደሚካኤል የስንብት ደብዳቤ ደርሷቸው ነው።
የቀድሞው የልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ከቦታቸው በተሻሩበት ወቅት ከባንኩ የብድር ፖሊሲ ውጭ በሆነ መልኩ ለተወሰኑ ባለሀብቶች ተገቢ ያልሆነ ብድር በመስጠት ወቀሳ ሢሰነዘርባቸው ነበር።
የቀድሞው የባንኩ የብድር አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ታደሰ ከኃላፊነታቸው የተነሱት ደግሞ፣ አቶ ጌታሁን ናና-በአቶ ኢሳያስ ከተተኩ በኋላ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ነው።
የልማት ባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ናና – አምና አቶ ታደሰንና ሌሎች ሦስት ምክትል ፕሬዚዳንቶችን ሲያነሱ የሰጡት ምክንያት ፦“ማኔጅመንቱን በአዲስ ኃይል ማዋቀር እና አዳዲስ ፊቶችን ወደ አመራር ማምጣት” የሚል ነበር።
የጋዜጣው ምንጮች ግን አቶ ታደሰ የተነሱት፣ በብድር አሰጣጥ ዙሪያ በተፈጠረ ከፍተኛ ቅራኔ ሳቢያ እንደሆነ አመልክተዋል።
እነዚሁ ምንጮች የቀድሞው የባንክ ማኔጅመን ቡድን፣ ከባንኩ የብድር ፖሊሲ ባፈነገጠ መልኩ በርካታ ብድሮች እንዲሰጡ ወስኗል ይላሉ። በ1909 የተመሰረተው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በአሁኑ ወቅት በመላ ሀገሪቱ 110 ቅርንጫፎች አሉት።
እስካለፈው ዓመት ሰኔ ወር ድረስ ባንኩ የሰጠው ብድር 33 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ከዚህ መካከል 9ነጥብ 9 ቢሊዮን ብሩ ለውጭ ባለሀብቶች የተሰጠ ነው።
አቶ ኢሳያስን የተኩት አዲሱ ፕሬዚዳንት አቶ ጌታሁን ናና አንድ ዓመት ተኩል ያህል ካገለገሉ በኋላ ከሰሞኑ ለባንኩ የቦርድ አመራር በጡረታ ያሰናብታቸው ዘንድ የመልቀቂያ ደብዳቤ ያስገቡ ሲሆን፣ እስካሁን ቦርዱ በደብዳቤው ላይ አልፈረመበትም።