መሪጌታ እንደስራቸው አግማሴ እንዲለቀቁ የሰሜን ጎንደር ዞን ሀገረስብከት ጠየቀ

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 28/2010) ላለፉት 24 ዓመታት በእስር ላይ የሚገኙት መሪጌታ እንደስራቸው አግማሴ እንዲለቀቁ የሰሜን ጎንደር ዞን ሀገረስብከት ጽሕፈት ቤት ጠየቀ።

በ1986 እንደኢትዮጵያ አቆጣጠር ታፍነው የተወሰዱትና በሕይወት መኖራቸው ሳይታወቅ የቆዩት መሪጌታ እንደስራቸው በትግራይ ባዶ ስድስት በመባል በሚታወቀው እስር ቤት ውስጥ እንደሚገኙ በቅርቡ መረጃ መውጣቱን ተከትሎ ነጻ እንዲወጡ የሚጠይቅ ግፊት ከየአቅጣቸው በመደረግ ላይ ነው።

በቤተክርስቲያኒቱ የትምህርት ደረጃ ከፍተኛ ቦታ ያላቸው እኚህ ሊቅ በአስቸኳይ ተፈተው ቤተሰቦቻቸውን እንዲቀላቀሉ የሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ጽሕፈት ቤት ለፓትሪያርኩ አቡነ ማቲያስ በጻፈው ደብዳቤ ጠይቋል።

ከ24 ዓመት በፊት ከሌሎች ሰዎች ጋር ታፍነው ወደ ትግራይ ባዶ ስድስት ጨለማ እስር ቤት የተወሰዱት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መምህርና ሊቅ መሪጌታ እንደስራቸው አግማሴ በህይወት መኖራቸው የታወቀው በቅርቡ ነው።

አብረዋቸው ታፍነው የተወሰዱት ሰዎች በሙሉ የተገደሉ ሲሆን እሳቸው በህወሃት እጅ ከወደቁበት ጊዜ አንስቶ ይኑሩ፡ ይገደሉ ሳይታወቅ 24 ዓመታትን ቆይተዋል።

መሪጌታ እንደስራቸው በህይወት መኖራቸው ከታወቀበት ካለፈው ሚያዚያ ወር አንስቶ እንዲፈቱ የሚጠይቁ እንቅስቃሴዎች በመደረግ ላይ ናቸው።

በውጭ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ መግለጫ በማውጣት የሃይማኖት ሊቁ እንዲፈቱ መጠየቁ የሚታወስ ነው።

የቤተክርስቲያኒቱ የተለያዩ የሃይማኖት አባቶችና መምህራንም መንግስት የሃይማኖት ሊቁን ከእስር ነጻ እንዲወጡ ግፊት በማድረግ ላይ እንዳሉ ለማወቅ ተችሏል።

በሀገር ቤት የሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በጉዳዩ ላይ ዝምታን መርጦ መቆየቱ በሚያነጋግርበት በዚህን ወቅት የሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ጽሕፈት ቤት የመሪጌታ እንደስራቸው አግማሴን መፈታት በመጠየቅ በይፋ የዘመቻው አካል መሆኑን አሳይቷል።

የሀገረ ስብከቱ ጽሕፈት ቤት ለብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ በጻፈው ደብዳቤ ላይ እንዳስታወቀው በቤተክርስቲያኒቱ የዜማ እውቀታቸው ላቅ ያለ ደረጃ የደረሱት መሪጌታ እንደስራቸው 24 ዓመታት በእስር መቆየታቸው በሀገረ ስብከቱ በሚሰጠው አገልግሎት ላይ ጉዳት አስከትሏል።

መሪጌታ እንደስራቸው ካላቸው የቤተክርስቲያኒቱ ዕውቀት አንጻር መተኪያ የሌላቸውና በተለይም በዜማና በተክሌ አቋቋም ያላቸው ከፍተኛ እውቀት፣ እንዲሁም እንደሌሎቹ የቤተክርስቲያኒቱ ሊቃውንት የራሳቸው የዜማ ድርሰት ያዘጋጁ ታላቅ ሊቅ ናቸው ሲል ሀገር ስብከቱ በደብዳቤው ገልጿል።

እንዲህ ዓይነት የሃይማኖት ሊቅ ያለጥፋቱ፡ ክስ ሳይመሰረትበት ለ24 ዓመታት በእስር ቤት መቆየት አይገባውም ያለው የሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት እኚህ አባት ለቤተክርስቲያናችን በዚህ ዘመን የተሰጡ የቅዱስ ያሬድና የአለቃ ተክሌ ምትክ ናቸው በማለትም ሚናቸውን አሳይቷል።

የመሪጌታ እንደስራቸው ከእስር መለቀቅ ለቤተክርስቲያኒቱ አገልግሎት ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ታምኖ በአስቸኳይ ከእስር መለቀቅ እንዳለባቸው የሰሜን ጎንደር ሀገር ስብከት ጽሕፈት ቤት በደብዳቤው ጠይቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በጀመሩት መልካም ተግባር ቀጥለው እኚህን የቤተክርስቲያናችንን ሊቅ እንዲፈቱ ያደርጉ ዘንድ ለብጹዕ ቅዱስ አቡነ ማቲያስ በጻፈው ደብዳቤ ላይ ተመልክቷል።

እኚህን የሃይማኖት ሊቅ ለ24 ዓመት በእስር ማቆየት የቤተክርስቲያናችንን ጉባዔ ቤት እንደመዝጋት የሚቆጠር በመሆኑ ፓትርያርኩ ከሚመለከተው የመንግስት አካል ጋር ተነጋግረው መሪጌታ እንደስራቸው አግማሴን ከእስር ነጻ እንዲያደርጉ ሀገረ ስብከቱ በአጽንዖት መጠየቁም ታውቋል።

በዚህ ጉዳይ ላይ ከፓትርያርኩም ሆነ ከቤተክርስቲያኒቱ እስካሁን የተሰጠ ምላሽ የለም።