የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያበደረው ገንዘብ 400 ቢሊየን ብር ደረሰ

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 28/2010) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለመንግስት ፕሮጀክቶች ያበደረው ገንዘብ 400 ቢሊዮን ብር ደረሰ።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምንጮች ለኢሳት እንደገለጹት ከቁጥጥር ወጭ የሄደው ብደር እና ክፍያው በአግባቡ አለመፈጸሙ የባንኩን ጤናማነት በከፍተኛ ደረጃ እየጎዳው መሆኑም ተመልክቷል።

ከፍተኛውን ብድር የወሰዱት የኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን እና የስኳር ኮርፖሬሽን እንዲሁም ሜቴክ መሆናቸውም ታውቋል።

የክልል መንግስታትም ከ5 ቢሊዮን እስከ 12 ቢሊየን ተበድረዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምንጮች ለኢሳት እንደገለጹት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሰራር ለመንግስት ፕሮጀክቶች የብድር ክፍያው ማጠናቀቂያ ግዜ ከ 5 እስከ 10 ዓመት ነው።

ነገር ግን ብዙዎቹ ፕሮጅርክቶች ብድራቸውን መመለስ ሳይጀምሩ የግዜ ገደቡ አልፏል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን የተበደረው ገንዘብ 273 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ይህም ለፊዚቢሊቲ (አዋጭነት) ጥናት እና ለአራቱ የግልገል ግቤ ሃይል ማመንጫዎች ግንባታ እንደሆነም ታውቋል።

ለእነዚህ የሃይል ማመንጫዎች ግንባታ መንግስት የውጭ ብድር መወሰዱም ተመልክቷል።

ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን 273 ቢሊዮን ብድር ሲበደር አብዛኛው ብድር የተወሰደው አቶ ግርማ ብሩ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን የቦርድ ሊቀመንበር እንዲሁም አቶ ምህረት ደበበ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በነበሩበት ወቅት ነው።

አቶ ግርማ ብሩ ከ 5 ዓመት በፊት በዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ከተተኩም በኋላ ብድሩ መቀጠሉ ተመልክቷል።

የአሁኗ የኮርፖሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አዜብ አስናቀ የተጋነነ የፊዚቢሊቲ ጥናት ወጪ በቀረበበት ሂደት ተሳታፊ እንደነበሩም ምንጮች ገልጸዋል።

ብድሩ በአጠቃላይ ወጪ የሆነው በተጋነነ ጥናት ላይ ተመርኩዞ እንደሆነም የባንኩ ምንጮች ገልጸዋል።

የአበዳሪው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ በቃሉ ዘለቀ  የተበዳሪው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን የቦርድ አባል መሆናቸው ከተጠያቂነት አንጻር ሕገወጥ ድርጊት መሆኑም ተመልክቷል።

ባንኩ ያልሰበሰበውን ብድር እና ወለድ እንደሚሰበስብ  ታሳቢ በማድረግ ብቻ የባንኩን ካፒታል እና ትርፍ ሪፖርት እንደሚያደርጉም መረዳት ተችሏል።

ስኳር ኮርፖሬሽን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የወሰደው ብድር 60 ቢሊዮን ብር የደረሰ  ሲሆን ፣ ከዚህ ውስጥ አብዛኛው ብድር የተወሰደው ፣አቶ አባይ ጸሃዬ የኮርፖሬሽኑ ዳይሬክተር እንዲሁም የአበዳሪው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቦርድ ሊቀመንበር በነበሩበት ወቅት ነው።

ብድሩ በአብዛኛው የተለቀቀው ለመስኖ እርሻ ፕሮጀክቶች ሲሆን ፣ከፍተኛውን የኮንትራት ስራ የወሰዱትና ተጠቃሚ የሆኑት የማነ ግርማይ የተባሉ የኮንስትራክሽን ድርጅት ባለቤት መሆናቸው ተመልክቷል።

እኒህ ሰው የአቶ አባይ ጸሃዬ የንግድ ሸሪክ መሆናቸውንም እነዚሁ ምንጮች ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ   ለነዚህ ፕሮጀክቶች የውጭ ብድር እንዲያገኙም ዋስትና መስጠቱ ተመልክቷል።

ያለበቂ ጥናት ለሚደረገው የውጭ ብድር የዋስትና ሂደት የባንኩ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሙሃመድ ኑረዲን እና ረዳታቸው አቶ ልኡል ጸሃዬ ዋና ተዋናይ መሆናቸው ተመልክቷል።አቶ ልኡል  ጸሃዬ የአቶ አባይ ጸሃዬ ወንድም ናቸው።

ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብድር  ሌሎች ከፍተኛ ብድር የወሰዱት አካላት የመሰረታዊ ብረታብረት ድርጅት ሜቴክ 12 ቢሊዮን ብር፣ኬሚካል ኢንደስትሪ 10 ቢሊዮን ብር እንዲሁም የአማራ ክልላዊ መንግስት 12 ቢሊዮን ብር፣የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት 9 ቢሊዮን ብር እንዲሁም የትግራይ ክልላዊ  መንግስት እና የደቡብ ክልላዊ መንግስት እያንዳንዳቸው 6 ቢሊዮን ብር ሲበደሩ፣የአዲስ አበባ አስተዳደር 5 ቢሊዮን ብር ተበድሯል።

እንዲሁም የኢትዮጵያ ኢንደስትሪ ግብአት ኮርፖሬሽን 3 ቢሊዮን ብር፣ወንጂ ስኳር ፋብሪካ 3 ቢሊዮን ብር በብድር ሲወስዱ የፊንጫ ስኳር ፋብሪካ ብድር 1.5 ቢሊዮን ደርሷል።

ከብድር አወሳሰዱና አመላለሱ  ጋር  ያለውን አሰራር ሕገወጥነት በተመለከተ የተደረገው ጥናት ሪፖርት በብሔራዊ ባንክ ሃላፊዎች እና በንግድ ባንክ የቦርድ አባላት ውድቅ መደረጉም ተመልክቷል።