በዳርፉር አመጽያን መሪ ግድያ ዙሪያ የኢትዮጵያ እጅ ሳይኖርበት እንደማይቀር መረጃዎች አመለከቱ

18 ቀን 2004 /

ኢሳት ዜና:-ለኢሳት የደረሰው የደህንነት መረጃ እንደሚያመለክተው የዳርፉር አማጺ መሪ የነበሩት ዶ/ር ካሊል ኢብራሂም ከመገደላቸው አንድ ቀን ቀደም ብሎ አቶ በረከት ስምኦን ከሱዳን ከፍተኛ የደህንነት ሰዎች ጋር በካርቱም ውይይት አድርገዋል።

አቶ በረከት ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ከ ኢትዮጵያ 10 የደህንነት አባላት ጋር ዲሰምበር 23 ቀን 11፡30 ላይ  በኢትዮጵያ አየር መንገድ ተሳፍረው ዲሰምበር 24 ቀን   ከቀኑ 6 ሰአት ከ55 ደቂቃ ላይ ካርቱም ደርሰዋል።

የካርቱም ከፍተኛ የደህንነት  ባለስልጣናትም አቶ በረከትን ተቀብለው አነጋግረዋቸዋል።

አቶ በረከት ካርቱም ካረፉ ከሰአታት በሁዋላ  የአመጽያኑ መሪ የሆኑት ዶ/ር ካሊል ኢብራሂም የመገደላቸው ዜና ለአለም ህዝብ ይፋ ሆኗል።

የፍትህና እኩልነት ንቅናቄ ቃል አቀባይ የሆኑት ጂብሪል አዳም ቢላል እንደተናገሩት፣ መሪያቸው የተገደሉት ከአውሮፕላን ላይ በተተኮሰ ሚሳኤል ነው። የሱዳን የመከላከያ ሚኒስትር አብዱል ራሂም ሙሀመድ በበኩላቸው ፣ ዶ/ር ካሊል ከአየር ላይ በተተኮሰ ሚሳኤል የተገደሉ መሆኑን አምነው ፣ ግድያው የተፈጸመው ግን የሱዳን የመከላከያ ሀይል ባካሄደው የስልክ ጠለፋ እንጅ  በውጭ እርዳታ አይደለም  ብለዋል።

ጂብሪል አዳም እንዲህ አይነቱን ድርጊት ለመፈጸም የአካባቢና አለማቀፍ ሀይሎች ተባብረዋል ሲሉ  ለቢቢሲ ዜና አግልግሎት ተናግረዋል።

ቃል አቀባዩ የአካባቢና የአለማቀፍ ሀይሎች ተሳትፈዋል ቢሉም የአገሮችን ስም  ከመጥቀስ ግን ተቆጥበዋል።

በርካታ የአማጽያኑ ደጋፊ የሆኑ ጋዜጠኞች ሰው አልባ በሆነ የጦር ጀት እንዲገደሉ ሁለት ጎረቤት አገሮች አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን እየዘገቡ ነው ሲል ሱዳን ትሪቢውን ዛሬ ባወጣው ዘገባ ጠቅሷል።

የኢሳት ምንጮች እንደሚሉት የኢትዮጵያ ጦር የ ዶ/ር ካሊልን  አጠቃላይ እንቅስቃሴ የተመለከተ የደህንነት መረጃ ለሱዳን መንግስት አሳልፎ ሰጥቷል።

የሁለቱ አገሮች ልኡካኖች በ14ኛው የድንበር ውይይት ወቅት በአማራ ክልል ዋና ከተማ ባህርዳር ከተማ ተገናኝተው በድንበር አካባቢ ያለውን የሁለቱን አገሮች አማጽያን እንቅስቃሴን ለመቆጣጠር ስምምነት ላይ መድረሳቸው ይታወሳል።

ይህን ተከትሎም  የመለስ መንግስት በኩርሙክ አካባቢ ሲንቀሳቀስ የነበረውን የሱዳን ነጻ አውጪ ጦር ወደ ኢትዮጵያ ድንበር እንዳይሻገር በመዝጋት በሱዳን መንግስት ጦር ሀይሎች ጥቃት እንዲደርስበት አድርጓል።

በአሁኑ ጊዜ በሰላም አስከባሪ ስም በዳርፉርና በደቡብ ሱዳን አቤየ ግዛት ውስጥ  ከፍተኛ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ጦር፣ በሰራው ስራ ከደቡብ ሱዳን፣ ከዳርፉር አምጸያንና የዳርፉር አማጽያንን ከሚደግፉት ፈረንሳይና እንግሊዝ ተቃውሞ ሊመጣበት ይችላል ተብሎአል።

የሰላም አስከባሪ ሀይሉ የትኛውንም ወገን መደገፍ እንደሌለበት እየታወቀ ፣ የመለስ መንግስት ከሱዳን መንግስት ጋር የመረጃ ልውውጥ ለማድረግ ስምምነት ላይ መድረሱ ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ድንጋጌ የሚጥስ ሆኖ ተገኝቷል።

ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉት የደህንነት ምንጮች እንደገለጡት  ከሆነ የኢትዮጵያ መንግስት የአለማቀፍ ስምምነትን በመጣስ ከሱዳን መንግስት ጋር የመረጃ ልውውጥ ለማድረግ የተገደደውና ለዶ/ር ካሊል ኢብራሂም ሞት ምክንያት የሆነው የኢትዮጵያ አማጽያን በሱዳን ድንበር በኩል የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ስጋት ውስጥ  ስለከተተው ነው።

የሱዳን መንግስት ተቃዋሚ  የሆኑት ተዋቂው  ዶ/ር አልቱራቢበሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ዶ/ር ካሊል የነጻነት ጀግና ነበሩ ሲሉ አወድሰዋቸዋል።

የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ጄኔራል አልበሽር በበኩላቸው ዶ/ር ካሊል ለፈጸሙት ግድያ አላህ ተበቀላቸው ሲል ለወታደሮቻቸው ንግግር አድርገዋል

በሱዳን የአሜሪካ መንግስት  ልዩ ልኡካን የሆኑት ፕሪስተን ሊይማን እና የዳርፉር አማካሪያቸው ዳኒ ስሚዝ ለንቅናቄው መሪዎች ሀዘናቸውን ገልጠዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ አቶ በረከት ስምኦን  የኢትዮጵያ መንግስት ለሱዳን መንግስት ለዋለለት ውለታ በመልሱ፣ የኤርትራውን መሪ ኢሳያስ አፈወርቅን ለማስገደል ሱዳን እንድትተባበር ጥያቄ ሳያቀርብ እንዳልቀረ አንድ የሁለቱን አገሮች ግንኙነት በቅርበት የሚከታተሉ ሰው ለኢሳት ተናግረዋል።

ግለሰቡ እንደሚሉት አቶ በረከት ፣ ኢትዮጵያ ለሱዳን መንግስት ከፍተኛ ውለታ በመፈጸሙዋ፣ኢትዮጵያም በተራዋ ከሱዳን መንግስት ከፍተኛ ውለታ ትጠብቃለች፤ ይህ ከፍተኛ ውለታ የተባለውም የፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን ህይወት ሊሆን እንደሚችል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የኤርትራን፣ የሱዳንን እና የኢትዮጵያን መንግስታት መልሶች ለማግኘት ያደረግነው  ሙከራ አልተሰካም።