ወደወህኒ የተጋዙ አራት አብራሪዎች አሁንም ከእስር አልተለቀቁም ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 24/ 2010) የኢትዮጵያ አየር ሃይል አብራሪ የነበሩና ሥርዓቱን በመቃወማቸው ወደወህኒ የተጋዙ አራት አብራሪዎች አሁንም ከእስር እንዳልተለቀቁ ታወቀ።

የፖለቲካ እስረኞች እንዲሁም በሌብነት ወንጀል ተጠርጥረው የነበሩና የተፈረደባቸው ጭምር ከእስር በተለቀቁበት በአሁኑ ሰዓት አራቱ የበረራ ባለሙያዎች በዝዋይና በቃሊቲ ማረሚያ ቤቶች ይገኛሉ።

የመቶ አለቃ በሃይሉ ገብሬ በ1997 ምርጫ ማግስት በአዲስ አበባ ከተማና በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተካሄደውን ግድያ በመቃወም ሔሊኮፕተር በመያዝ ወደ ጅቡቲ በመብረር ጥገኝነት ጠይቆ ነበር፣

የጅቡቲ መንግስት ግን የአብራሪውን ጥገኝነት  ጥያቄ ወደ ጎን በማለት ለኢትዮጵያ መንግስት ተላልፎ እንዲሰጥ በማድረጉ የመቶ አለቃ በሃይሉ ገብሬ ወደ እስር ቤት ተወርውሯል።

በዚህም ምክንያት መቶ አለቃ በሃይሉ በተለያዩ የስቃይ ወህኒ ቤቶች አብሮት ጥገኝነት ከጠየቀው አብዮት ማንጉዳይ ጋር አሳልፏል።

በመጨረሻም የጦር ፍርድ ቤት ቀርቦ የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶበት ላለፉት 14 አመታት በእስር ቤት ውስጥ ቆይቷል።አሁንም በዝዋይ ወህኒ ቤት ይገኛል።

አብሮት ሔሊኮፕተር ይዞ የጠፋው የመቶ አለቃ አብዮት ማንጉዳይም የተወሰነበትን እስራት ጨርሶ ከወህኒ ከወጣ በኋላ በአሁኑ ወቅት በስደት ላይ መሆኑን መረዳት ተችሏል።

ከ1997 በኋላ በኢትዮጵያ የቀጠለውን አፈና በመቃወምና በአየር ሃይሉ ውስጥ ያለው የአንድ ብሔር የበላይነት ያብቃ በሚል በመንቀሳቀሳቸው በአሸባሪነትና በሃገር ክህደት ተከሰው ወህኒ የገቡት የመቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ፣የመቶ አለቃ ዳንኤል ግርማና የመቶ አለቃ አንተነህ ታደሰም ዛሬም በቃሊቲና በዝዋይ ወህኒ ቤት ውስጥ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል።

የመቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤና የመቶ አለቃ ዳንኤል ግርማ በተመሰረተባቸው ክስ እያንዳንዳቸው የ10 አመት እስራት ቢፈረድባቸውም ፍርዱ ግን በይቅርታ ተነስቷል ተብሏል።

ሆኖም በቃሊቲ ወህኒ ቤት ቃጠሎ ሳቢያ እንደገና ክስ እንዲመሰረትባቸው ተደርጓል።

ይህም ክስ በይቅርታ ቢነሳላቸውም ውሳኔው ተግባራዊ ባለመሆኑ በዝዋይና በቃሊቲ ወህኒ ቤት ያለምንም ሕጋዊ አግባብ ታስረው እንደሚገኙ ተመልክቷል።

የመቶ አለቃ ዳንኤል ግርማ በቃሊቲ ወህኒ ቤት ቃጠሎ ወቅት ፖሊሶች በከፈቱት ተኩስ እግሩን በጥይት እንደተመታም መረዳት ተችሏል።

የመቶ አለቃ አንተነህ ታደሰ በተመሰረተበት የሽብርና የሀገር ክህደት ክስ 5 አመት ከ6 ወር ተፈርዶበት ዛሬም በወህኒ ይገኛል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም  ፍቅረማርያም አስማማው እና ቤተሰብ ለመጠየቅ ከለንደን ወደ አዲስ አበባ በመጓዝ በአሸባሪነት ተከሶ ወህኒቤት የገባውን አቶ አበበ ወንድማገኝ ጨምሮ አሁንም በርካታ የፖለቲካ እስረኞች  በወህኒ ቤት መኖራቸውን መረዳት ተችሏል።