አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በእንግሊዝ ለንደን ደማቅ አቀባበል ተደረገላቸው

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 24/ 2010) በቅርቡ ከእስር የተልቀቁት አቶ አንዳርጋጨው ጽጌ እንግሊዝ ለንደን ሲገቡ በአውሮፓና አካባቢው በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ደማቅ አቀባበል ተደረገላቸው።

አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ለአራት ዓመታት በእስር ምክንያት ከተለያዩቸው ባለቤታቸውና ልጆቻቸው ጋር በሰላም መገናኘታቸውም ታውቋል።

ኢትጵያውያኑ ላደረጉላቸው አቀባበልም ሆነ እርሳቸው ከእስር እንዲፈቱ ላደረጉት ጥረት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል።

ፍቺውን ለማስተጓጎል የተደረገው ሙከራ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መክሸፉንም አቶ አንዳርጋቸው ለንደን ላይ ተናግረዋል።

“እኔ አላማ አስፈጻሚ እንጂ አላማ አይደለሁም።”አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ለንደን ሲደርሱ እጅግ በርካታ ኢትዮጵያውያን ሲቀበሏቸው የተናገሩት ነው።

አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ “ላንቺ ነው ኢትዮጵያ” በሚል የጻፉትን ግጥም መነሻ በማድረግ የሚዜመውን ሙዚቃ እያስተጋቡ ኢትዮጵያውያን በሒትሮ አውሮፕላን ማረፊያ ለንደን ደማቅ አቀባበል አድርገዋል።

በአቀባበል ስነስርአቱ ኢትዮጵያውያን በሆታና በለቅሶ ደስታቸውንና ቁጭታቸውን ሲገልጹ ጋዜጠኞች፣አክቲቪስቶችና ቤተሰቦቻቸውም በስፍራው ነበሩ።

አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ባለቤታቸውንና ልጆቻቸውን ሲያገኙም በእንባና በደስታ ታጅበው ነበር።

አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከእስር እንዲፈቱ ኢትዮጵያውያን ላደረጉት ጥረትና ለተደረገላቸው አቀባበልም ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል።

በዚሁ ንግግራቸው ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሃገርን ለማዳን በሚደረገው ጥረት አላማው እስኪሳካ ድረስ ትግሉን እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።–“እኔ አላማ አስፈጻሚ እንጂ አላማው አይደለሁም በማለት”

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ከሁለት ቀን በፊት ለአንድ ሰዓት ተኩል ያህል ተነጋግሪያለሁ  በማለት ሂትሮ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ ለውጭ መገናኛ ብዙሃን መግለጫ የሰጡት  አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በሃገሪቱ  ውስጥ ያለው የለውጥ ሁኔታ ለመፈታታቸው ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል

እኔን ለማስፈታት በገዢው ፓርቲ ወስጥ ትግል ተደርጓል ያሉት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በዚህ ሂደት  የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ሚና  ከፍተኛ እንደነበር መረዳታቸውንም አክለዋል።

እኔን በመፍታት የሚመጣባቸውን ችግር ለመቀበል ወስነው የወሰዱት ርምጃ ነው ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬዛ ሜይ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከእስር በመለቀቃቸው ለኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ምስጋና አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬዛ ሜይ ከኢትዮጵያው አቻቸው ዶክተር አብይ አሕመድ ጋር የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌን መልቀቅ በተመለከተ የስልክ ውይይት ማድረጋቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።