(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 23/2010) ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ በኢትዮጵያውያን ፌስቲቫል ላይ እንዲገኙ የቀረበውን ጥያቄ አለመቀበሉን የሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያውያን እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታወቀ።
31 አባላት ያሉት የፌዴሬሽኑ ቦርድ ጥያቄውን ያልተቀበለው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ቢጋበዙ ቀሪው ጊዜ አጭር በመሆኑ ሊፈጠር የሚችለውን የሰው ብዛት መጨናነቅና የቦታ ጥበት ምክንያት በማድረግ ነው ብሏል።
እናም የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ጥያቄ ለሚቀጥለው አመት ቢቀርብ ጉዳዩን እንደገና እንደሚያጤነው ፌዴሬሽኑ አስታውቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ በየአመቱ በሚካሄደው የኢትዮጵያውያን ፌስቲቫል ላይ ለመገኘት ለሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያውያን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጥያቄው የቀረበው በዋሽንግተን የኢትዮጵያ አምባሳደር አቶ ካሳ ተክለብርሀን በኩል ነበር።
ጥያቄው መቅረቡን ተከትሎም በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይጋበዙ ወይንስ አይጋበዙ በሚል ክርክር ሲያደርጉ ቆይተዋል።
ፌዴሬሽኑ ጥያቄውን ሊቀበል እንደሚችል ፍንጭ በመስጠቱ በጉዳዩ ላይ ድጋፍና ተቃውሞ ሲሰማ ሰንብቷል።
31 አባላት ያሉት የሰሜን አሜሪካ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ቦርድ ጉዳዩን ሲያብላላና ሲመክር ከቆየ በኋላ በመጨረሻ ጥያቄውን እንዳልተቀበለው የሚገልጽ መረጃ በደረገጹ ላይ አውጥቷል።
ፌዴሬሽኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በዝግጅቱ ላይ እንዲገኙ የቀረበውን ጥያቄ ያልተቀበለበትን 3 ምክንያቶች በመግለጫው አመልክቷል።
የመጀመሪያው ምክንያት ጥያቄው ዝግጅት ሊካሄድ በተቃረበበት ጊዜ የቀረበ በመሆኑ ሊገኝ የሚችለውን የሰው ብዛት በማሰብ የተሳታፊዎችንና የእንግዶችን ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል ነው።
ስነስርአቱ የሚካሄድበት ቦታ ጠባብ በመሆኑም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢገኙ ሊፈጠር የሚችለው መጨናነቅም ሁለተኛው ምክንያት ሆኖ ተወስዷል።
ከኢንሹራንስ ጉዳይ ጋር የተያያዙ ስራዎች ቀድመው በመጠናቀቃቸው እንደገና ጉዳዩን ለመጀመር ጊዜ አለመኖሩም 3ኛው ምክንያት እንደሆነ ፈዴረሽኑ ገልጿል።
የሰሜን አሜሪካ ኢትዮጵያውያን እግር ኳስ ፌዴሬሽን በሃገሪቱ እየተካሄደ ያለውን ለውጥ በአዎንታዊነት እንደሚመለከተው አስታውቋል።
እናም ሰላማዊ ውይይቱ እንዲጠናከር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድን ጨምሮ ሁሉም ወገኖች በጎ ጥረታቸውን እንዲደገፉበት ፌዴሬሽኑ ጥሪ አቅርቧል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በኢትዮጵያ ፌስቲቫል ላይ እንዲገኙ የቀረበውን ጥያቄ ፌዴሬሽኑ ወደፊት እንደገና እንደሚያጤነው አስታውቋል።