ከቤንሻንጉል ጉሙዝና ኦሮምያ ክልል የተፈናቀሉ የአማራ ተወላጆች የመፍትሄ ያለህ እያሉ ነው

ከቤንሻንጉል ጉሙዝና ኦሮምያ ክልል የተፈናቀሉ የአማራ ተወላጆች የመፍትሄ ያለህ እያሉ ነው
(ኢሳት ዜና ግንቦት 22 ቀን 2010 ዓ/ም) በመቶዎች የሚቆጠሩ ከቤንሻንጉል ጉሙዝና ከኦሮምያ ክልል ቡኖ በደሌ ወረዳ የተፈናቀሉ የአማራ ተወላጆች በአሁኑ ሰዓት በባህርዳር ከተማ በጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን እንዲሁም በተለምዶ አባይ ማዶ እየተባለ በሚጠራው በምግብ ዋስትና ግቢ ውስጥ ተጠልለው ይገኛሉ። በምግብ ዋስትና ግቢ ውስጥ ተጠልለው የሚገኙት ተፈናቃዮች፣ ከሳምንታት በፊት ወደ ትውልድ ቀያቸው እንዲሄዱ ቢደረግም፣ በቦታው ሲደርሱ የዞኑ አስተዳዳሪዎች ሊቀበሉዋቸው እንዳልቻሉና ተመልሰው ወደ ባህርዳር መሄዳቸውን ተፈናቃዮች ተናግረዋል።
የአማራ ክልል አስተዳደር ተፈናቃዮች ወደ መጡበት ክልል እንዲመለሱ ወይም ወደ ተወለዱበት ቀዬ ሄደው እንዲኖሩ ሃሳብ ማቅረቡ ይታወቃል። ተፈናቃዮች ወደ ተፈናቀሉበት ክልል መመለስ እንደማይልጉ፣ ክልሉ መሬት ከሰጣቸው በየትኛውም ቦታ ሄደው መስራት እንደሚችሉ ሲገልጹ ቆይተዋል።