(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 22/2010) በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ መፈታት ደስታቸውን በመግለጽ ላይ መሆናቸው ታወቀ።
በአውሮፓ፣ በአውስትራሊያ፣ በአሜሪካ፣ በካናዳ፣ በደቡብ አፍሪካ፣ በእስራኤልና በሌሎች የዓለም ክፍሎች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ስነስርዓቶች ደስታቸውን እየገለጹ መሆናቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
በሌላ በኩል በጓዳችን መፈታት ደስ ብሎናል፤ የሚጠብቀን ብዙ መሆኑን እናውቃለን ሲል አርበኞች ግንቦት ሰባት መግለጫ አውጥቷል።
የአቃቤ ህግ መግለጫ ከተሰጠበት ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ የኢትዮጵያውያን አይንና ጆሮ ወደ ቃሊቲ እስር ቤት ተተክለው ነበር ያለፉትን አራት ቀናት ይቆዩት።
በመላው አለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌን መፈታት፡ በሰላማዊ ሰልፍና በተለያዩ እንቅስቃሴዎች ሲጠይቁ ቆይተዋል።
ሰሞኑን እንደሚፈታ ከተገለጸበት ቀን ጀምሮ አቶ አንዳርጋቸውን በአካል ወጥተው ለማየት በጉጉት ሲጠባበቅ ነበር።
ትላንት በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከቀትር በኋላ አቶ አንዳርጋቸ ጽጌን የጫነችው የፖሊስ መኪና ቦሌ ከሚገኘው የአባቱ መኖሪያ ቤት ስትደርስ በመላው ዓለም ኢትዮጵያውያን በቀጥታ ይከታተሉት ነበር።
አቶ አንዳርጋቸው ከአራት አመት እስራት በኋላ ከቤተሰቦቻቸውና ከደጋፊዎቻቸው ጋር በአካል ሲገናኙ ስሜቱ ልዩ እንደነበረ ከአዲስ አበባ ሲተላለፍ ከነበረው የቀጥታ ስርጭት መከታተል ተችሏል።
ይህ ስሜት በመላው ዓለም በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ የተንጸባረቀ ሲሆን በተለያዩ ስነስርዓቶች የአንዳርጋቸው ጽጌን መፈታት በልዩ የድስታ ስሜት ተቀብለውታል።
በሲውዲን ኢትዮጵያውያን ተሰባስበው ድስታቸውን የገለጹ ሲሆን በኖርዌይ ኦስሎ፡ በስዊዘርላንድ በርን፡ በጀርመን፡ በካናዳ ቶሮንቶና ካልጋሪ፡ በአሜሪካን በበርካታ ከተሞች ኢትዮጵያውያን በልዩ ሁኔታ ዕለቱን በደስታ አሳልፈውታል።
በዋሽንግተን ዲሲ የአርበኞች ግንቦት ሰባት ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በተገኙበት የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ መፈታትን በተመለከተ የተዘጋጅ ልዩ ፕሮግራም ተካሂዷል።
በእስራኤል በደቡብ አፍሪካ እንዲሁ ኢትዮጵያውያን ደስታቸውን በመግለጽ ለአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የዓላማ ጽናት ያላቸውን አክብሮት አሳይተዋል።
ዛሬም በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ኢትዮጵያውያን ተመሳሳይ ፕሮግራሞች በመካሄድ ላይ ናቸው።
በሌላ በኩል አርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ መፈታትን በተመለከተ መግለጫ አውጥቷል።
በጓዳችን መፈታት ደስ ብሎናል፣የሚጠብቀን ብዙ ስራ እንዳለ እናውቃለን በሚል ርዕስ ንቅናቄው ባወጣው መግለጫ ይህ እውን እንዲሆን ጥረት ላደረጉ ኢትዮጵያዊያንን ዜጎች እና የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ድርጅቶች እንዲሁም ከጎናችን ለቆሙ የውጭ አገር ዜጎችና ድርጅቶች ሁሉ ከፍተኛ ምስጋና ያቀርባል ሲል አስታውቋል።
ደስታችን የተሟላ የሚሆነው ግን ወገኖቻችን የሞቱለት፣ የታሰሩለት፣ የተሰደዱለትና የተሰቃዩበት ዓላማ ሲሳካ ነው።
ዛሬም አቶ አበበ ካሴ፣ ሰይፉ አለሙ፣ ፍቅረማርያም አስማማው፣ ማስረሻ ሰጤ፣ መስፍን አበበ፣ አበበ ኡርጌሳ፣ ራቪድ ሳላ እና ሌሎች በርካታ ወገኖቻችን በእስር ላይ ይገኛሉ።
ለእነዚህ ሁሉ ወገኖቻችን ነፃነት የምናደርገው ትግል አጠናክረን መቀጠል ግዴታችን መሆኑን እንገነዘባለን ሲል አርበኞች ግንቦት ሰባት በመግለጫው ገልጿል።
በጓዳችን አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ መፈታት ምክንያት ደስታችን ከፍተኛ ቢሆንም ከእንግዲህ የሚጠብቀን ትግል ከዚህ በፊት ከነበረው የበለጠ መስዋትነት ሊጠይቅ የሚችል መሆኑን በመገንዘብ ተዘጋጅተናል።
እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የሀገሩ ባለሙሉ መብት ዜጋ እስኪሆን ትግላችንን እንቀጥላለን በማለት ንቅናቄው በመግለጫው አስታውቋል።