ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋና ጃዋር መሀመድ ላይ ተመስርቶ የነበረው ክስ ተቋረጠ

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 21/2010) አቃቤ ሕግ በአርበኞች ግንቦት 7 ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋና ጃዋር መሀመድ ላይ መስርቶት የነበረውን ክስ ማቋረጡ ተነገረ።

በሁለት መገናኛ ብዙሃን ማለትም በኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥንና ሬዲዮ (ኢሳት) እና በኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ (ኦ ኤም ኤን)፣ ላይ አቅርቦት የነበረውን ክስም አቃቤሕግ ማንሳቱ ታውቋል።

ይሕ በእንዲህ እንዳለ ግን በአርበኞች ግንቦት 7 ስም የተከሰሱ በርካታ ተከሳሾች ክስአሁንም አልተቋረጠም።

የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በእነ ዶክተር መረራ ጉዲና ክስ መዝገብ በሁለት መገናኛ ብዙሃንና ሁለት ታዋቂ ግለሰቦች ላይ አቅርቦት የነበረውን ክስ ማንሳቱን ምንጮች ገልጸዋል።

በእነ ዶክተር መረራ ክስ መዝገብ የሽብር ክስ ተመስርቶባቸው የነበሩት የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን (ኢሳት)፣ የኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ (ኦ ኤም ኤን)፣ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እና ጃዋር ሞሃመድ ክሳቸው ተቋርጧል።

ሁለቱ ታዋቂ ሰዎች በሌሉበት በሽብር ወንጀል መከሰሳቸው አይዘነጋም።

የዶክተር መረራ ጉዲና ክስ ቀደም ብሎ በመቋረጡ ከእስር መለቀቃቸው ይታወሳል።

ዐቃቤ ሕግ የ137 ተከሳሾችን ክስ እንዳነሳ ነው የተገለጸው።

ይሕ በእንዲህ እንዳለ ግን በግንቦት 7 ተከሰው በማዕከላዊ ስቃይ የደረሰባቸው፣ ብልታቸው የተኮላሸው አስቻለው ደሴ እና ዮናስ ጋሻው ክሳቸው እንዳልተቋረጠ ለማወቅ ተችሏል።

በተያየዘም የጎንደር ዩኒቨርስቲ መምህሩ ጌታ አስራደን ጨምሮ የበርካታ አማራ ተወላጆች ክስ አለመቋረጡን ምንጮች ገልፀዋል።

በአሁኑ ወቅት በእስር ላይ ያሉትን ክስ ከማቋረጥ ይልቅ ቀደም ብሎ ክሳቸው የተቋረጠላቸውን ስም በማካተት የብዙ ተከሳሾች ክስ እንደተቋረጠ ነው የተነገረው።

ከአሁን ቀደም ከእስር የተፈቱን አስቻለው አብርሃምና ሌሎች ተከሳሾችን ስም በማካተት ዐቃቤ ሕግ  ክሳቸውን አቋርጫለሁ ማለቱ የቁጥር ማሟያ ለማድረግ ነው መባሉን አዲስ አበባ የሚገኙ ምንጮች ገልጸዋል።