በአርባምንጭ ከተማ በፌደራል ፖሊስና በነዋሪው መካከል ግጭት ተፈጠረ

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 17/2010)በአርባምንጭ ከተማ በፌደራል ፖሊስና በነዋሪው መካከል ግጭት መፈጠሩ ተገለጸ።

ጉርባ በተሰኘው የከተማው ክፍል መኖሪያ ቤቶችን ለማፍረስ የተሰማራውን ግብረሃይል ነዋሪው ማስቆሙን ተከትሎ በመከላከያ ሰራዊት ድጋፍ ወደ ጉርባ የገባው የፌደራል ፖሊስ ህዝቡ ላይ መተኮሱን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

ከ20 በላይ ሰዎች መጎዳታቸውም ታውቋል።

ከ4ሺህ በላይ ነዋሪ በላዩ ላይ ቤት መፍረሱ ሌላውን የአርባምንጭ ከተማ ነዋሪን እንዳስቆጣም ለማወቅ ተችሏል።

ሻራ በተሰኘውም መንደር በተመሳሳይ የአፍራሽ ግብረ ሃይል መሰማራቱ ታውቋል።

ጉርባ በአርባምንጭ ከሚገኙ መንደሮች አንዱ ነው። አካባቢው በቀድሞው መንግስት ለወታደራዊ ካምፕ አገልግሎት እንዲውል ታስቦ እንደነበረ ይነገራል።

ይሁንና የህወሃት አገዛዝ ስልጣን ከያዘ ወዲህ በአካባቢው በህጋዊ መንገድ ሰዎች መኖሪያ ቤት ገንብተው የሞቀ መንደር አድርገውት ቆይተዋል።

ላለፉት 20 ዓመታት ጉርባ በተሰኘው መንደር መኖሪያቸውን ቀልሰው ልጅ ወልደው ቤተሰብ መስርተው የሚኖሩት ከ4ሺህ በላይ አባወራዎች ህጋዊ በሆነ መንገድ የመብራትና የውሃን ጨምሮ የተለያዩ ክፍያዎችን ሲፈጽሙ ቆይተዋል።

የቀበሌም ሆነ የከተማ አስተዳደሩ ከህጋዊነት ጋር በተያያዘ የተነሳባቸው ጥያቄ እንዳልነበረ የሚገልጹት ነዋሪዎቹ ቤታቸው እንዲፈርስ መወሰኑ ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንዲወድቁ እንዳደረጋቸው በስሜት ይናገራሉ።

የከተማው አስተዳደር በህገወጥ መንገድ የሰራችሁት ቤት በመሆኑ አፍርሳችሁ አካባቢውን ልቀቁ የሚል ውሳኔ ሲሰጥ ምትክ ቦታ አላዘጋጀላቸውም።

ነዋሪዎች በተለያዩ ተጽእኖዎች አካባቢውን እንዲለቁ የከተማው አስተዳደር ሙከራዎች እንዳደረገም ተገልጿል።

በተለይም የውሃና የመብራት መስመሮችን በመቁረጥ ነዋሪው ተገፍቶና ተስፋ ቆርጦ በራሱ ጊዜ አካባቢውን ለቆ እንዲሄድ ታስቦ እንደነበርም የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

ነዋሪው በዚህም እጅ ሳይሰጥ ቦታውን ይዞ ቆይቷል። በመጨረሻም ዛሬ አፍራሽ ግብረ ሃይል በፌደራል ፖሊስና በመከላከያ ሰራዊት ታጅቦ ወደ ጉርባ መንደር መዝመቱን ነው ለማወቅ የተቻለው።

ሌሊቱን ነዋሪው በእንቅልፍ ላይ እያለ ቤቱን ላዩ ላይ ማፍረስ የጀመረው ግብረ ሃይል ከፍተኛ ግጭት ውስጥ ገብቷል።

በሌሊት ቤቱን ለማፈረስ በዘመተው ሃይል ላይ ድንጋይና የተለያዩ ራስን መከላከያ መሳሪዎችን በመያዝ የተጋፈጠው ነዋሪው ለሰዓታት የዘለቀ ግጭት ውስጥ መግባቱን የጠቀሱት የኢሳት ምንጮች የፌደራል ፖሊስ ጥይት በብዛት በመተኮስ ለማስቆም ጥረት ሲያደርግ ነበርም ተብሏል።

በግጭቱ ከ20 በላይ ነዋሪዎች ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው ታውቋል።

ከ4ሺህ በላይ አባዎራዎች ከነቤተሰቦቻቸው በአንድ ሌሊት ቤት አልባ ያደረጋቸው የዛሬው ርምጃ በአርባምንጭ ነዋሪዎች ዘንድም ቁጣን መቀስቀሱ እየተነገረ ነው።

ሰው የጉርባ ነዋሪን መፈናቀል ለማስቆም በመነጋገር ላይ ነው ሲሉ የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

የተኩስ እሩምታው ለሰዓታት እንደዘለቀ የሚገልጹት ምንጮች አካባቢው በከፍተኛ ውጥረት ውስጥ እንደዋለም ጠቅሰዋል።

ጉዳዩን በተመለከተ ምላሽ እንዲሰጡን ወደ ከተማው አስተዳደር አመራሮች ጋር ስልክ ብንደውልም ሙከራችን አልተሳካም።

ወደ አካባቢው የሚወስደው መንገድ የተዘጋ ሲሆን የፌደራል ፖሊስና መከላከያ የጉርባን መንደር ወረውት እንደሚገኙ የደረሰን መረጃ ያመለክታል።