የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሰሜን ኮሪያው አቻቸው ጋር ለመገናኘት የያዙትን ፕሮግራም ሰረዙ።

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሰሜን ኮሪያው አቻቸው ጋር ለመገናኘት የያዙትን ፕሮግራም ሰረዙ።
(ኢሳት ዜና ግንቦት 16 ቀን 2010 ዓ/ም) በደቡብ ኮሪያ ሸምጋይነት ነበር የሁለቱ ባላንጣ ሀገር መሪዎች ዶናልድ ትራምፕና ኪም ዮንግ አን ለመጀመሪያ ጊዜ በሚቀጥለው ሰኔ ወር አጋማሽ ላይ እንደሚገናኙ ሲጠበቅ የቆዬ ቢሆንም፣ ፒዮንግያንግ አንዳንድ ተጨማሪ ቅድመ ሁኔታዎችን ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆኗ እና በቅርቡ ያወጣችው ቁጣ አዘል መግለጫ ዋሽንግተንን ቅውር እንዳሰኘ ተመልክቷል።
በመሆኑም እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር የፊታችን ሰኔ 12 ሁሉቱ ባላንጣ መሪዎች በሲንጋፖር ለመገናኘት የተያዘላቸውን ፕሮግራም የአሜሪካው መሪ ሰርዘውታል።
ትራምፕ ፕሮግራሙን መሰረዛቸውን ተከትሎ ለኪም ዮንግ አን በጻፉት ደብዳቤ ወደ ፊት አንድ ቀን እንገናኛለን የሚል ተስፋ አለኝ ብለዋቸዋል።.
“በተያዘው ቀጠሮ ከእርስዎ ጋር ለመገናኘት በጣም ነበር የምፈልገው።ሆኖም ሀገርዎ ሰሞኑን ያወጣችውን ቁጣ የተቀላቀለበት መግለጫና ነቀፋ ስመለከት በአሁኑ ወቅት መገናኘታችን ተገቢ እንዳልሆነ እና ሌካ ረዘም ያለ ፕሮግራም መያዝ እንዳለብን ተረዳሁ” ብለዋል ትራምፕ-በዚሁ ለኪም በጻፉት ደብዳቤ ላይ።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት አክለውም፦”አንተ ስለ ኒዩክሌር ብቃታችሁ እያወራህ ነው።ይሁንና የኛ ከእናንተ እጅግ ኃያልና ብዙ ግዙፍ ነው። ጥቅም ላይ እንዳናውለው ለአምላክ እጸልያለሁ” በማለትም ለማስፈራራት ሞክረዋል።
እንደ ቢቢሲ ዘገባ፣ዶናልድ ትራምፕ ደብዳቤያቸውን የቋጩት ኪም ዮንግ አን የያዙትን አቋም ከቀየሩ፣ ሊደውሉላቸው እንደሚችሉ በማሥታወስ ነው።
ትራምፕ በጉዳዩ ዙሪያ በሰጡት መግለጫም “ዓለማችን በተለይም ሰሜን ኮሪያ የረዥም ጊዜ ሰላም፣ትልቅ ብልጽግና እና ሀብት አጥተዋል። ይህን ዕድል ማጣት በእርግጥ ታሪክ ታላቅ ክስተት ነው” ብለዋል።
ባለፈው ማክሰኞ የሰሜን ኮሪያው ባለሥልጣን ቾ ሶን ሁይ -የአሜሪካው ምክትል ፕሬዚዳንት ማይክ ፔንስ ሰሜን ኮሪያ የኑክሌር ፕሮግራሟን ልክ እንደ ሊቢያ ጨርሳ ማስወገድ አለባት ማለታቸውን ውድቅ ከማድረጋቸውም ባሻገር፣ የፔንስን አባባል ዋሽንግተን አሁንም በፒዮንግያንግ ላይ እያሴረች ለመሆኑ እንደ አስረጅ ጠቅሰዋል።
ጋዳፊ መወገዳቸውን ተከትሎ ሰሜን ኮሪያ በሰጠችው መግለጫ ሊቢያ የኑክሌር ፕሮግራሟን ጠቅላላ ባታስወግድ ኖሮ ጋዳፊ አማጽያኑ ከምዕራባውያን ወታደሮች ጋር በመተባበር ከከፈቱባቸው ጦርነት ማምለጥ ይችሉ ነበር ማለቷ ይታወሳል።