(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 16/2010) ሰማያዊ ፓርቲ ከተቋረጠው የድርድር ሂደት እንደገና እንዲመለስ ኢህአዴግ ጥሪ አቀረበ።
የኢሕአዴግ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር ለድርጅቱ በጻፉት ደብዳቤ ሰማያዊ ፓርቲ ወደ ድርድር ለመመለስ የመነሻ ሃሳብ እንዲያቀርብ ጠይቀዋል።
ሰማያዊ ፓርቲ በሰጠው ምላሽ ግን ገለልተኛ አደራዳሪ በሌለበት ውይይት ለመጀመር እንደማይፈልግ ገልጿል።
የኢሕአዴግ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ሚያዚያ 30/2010 ለሰማያዊ ፓርቲ በጻፈው ደብዳቤ የፖለቲካ ድርጅቱ ወደ ድርድር ተመልሶ እንዲገባና የመነሻ ሀሳቦችን እንዲያቀርብ ጠይቋል።
በኢሕአዴግ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚእብሄር የተጻፈው ደብዳቤ እንደሚያመለክተው ገዥው ፓርቲ ከሰማያዊ ፓርቲ ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ይፈልጋል።
እናም ሰማያዊ ፓርቲ ምላሹን በ 8 ቀናት ውስጥ ለኢህአዴግ እንዲሰጥ ጠይቋል።
ሰማያዊ ፓርቲ በበኩሉ ለኢሕአዴግ በሰጠው ምላሽ በኢትዮጵያ እውነተኛ ውይይትና ድርድር እንዲካሄድ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እንዲኖርም ፍላጎት እንዳለው ገልጿል።
ድርድሩ ግን የኢትዮጵያን ሕዝብ መሰረታዊ የለውጥ ጥያቄዎች በእርግጠኝነት ሊፈታ ይገባል ነው ያለው።
ይሕም በትጥቅ ትግል ላይ የሚገኙትንም እንዲጨምር ሰማያዊ ፓርቲ ፍላጎት እንዳለው ጠቁሟል።
ሰማያዊ ፓርቲ የእንደራደር ጥያቄውን በአዎንታዊነት እንደሚቀበለው ቢገልጽም ነጻና ገለልተኛ አስማሚ በሌለበት ግን ወደ ውይይት መመለስ እንደማይፈልግ አስታወቋል።
ኢሕአዴግ ያቀረበው የእንወያይ ጥያቄ በገለልተኛ አደራዳሪ የሚመራ ከሆነ ሰማያዊ ፓርቲ የመደራደሪያ መነሻ ሃሳቦችን ያቀርባል ብሏል።
በኢትዮጵያ የተከሰተውን ሕዝባዊ ታቃውሞ ተከትሎ በሀገሪቱ በሕጋዊ መንገድ የተመዘገቡ ፓርቲዎች ድርድር መጀምራቸው ይታወሳል።
ድርድሩ ከተጀመረ በኋላም ሰማያዊ ፓርቲ፣ ኢዴፓ እና ኢራፓ ቆይተው ከሂደቱ ራሳቸውን አገልግለዋል።
ፓርቲዎቹ ከዚህ ቀደም በገለልተኛ አደራዳሪ ውይይቱ እንዲካሄድ ጠይቀው በኢሕአዴግ በኩል ተቀባይነት አለማግኘቱ ይታወሳል።