በቴፒ ከተማ በአማራ ተወላጆች ላይ ጥቃት እየተፈጸመ ነው ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 16/2010)በቤንች ማጂ ዞን ቴፒ ከተማ የህዝቡን ተቃውሞ አቅጣጫ ለማስቀየስ በአማራ ተወላጆች ላይ ጥቃት እየተፈጸመ ነው ተባለ።

በዞኑና በዙሪያው ባሉ አካባቢዎች የመብት ጥያቄ በማንሳት የተጀመረው ተቃውሞ ሰሞኑን ተጠናክሮ በቀጠለበት ወቅት የአማራ ተወላጆችን ማጥቃትና ንብረታቸውን ማውደሙ ሆን ተብሎ በአገዛዙ የተፈጸመ ነው ሲሉ ኢሳት ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል።

የህዝቡ ጥያቄ የነጻነትና የሀብት ተጠቃሚነት በመሆኑ ትግሉ እንደሚቀጥል የገለጹት ነዋሪዎች የእርስ በእርስ ግጭት እንዲሆን የሚደረገው የአገዛዙ ሴራ ጥያቄያቸውን እንደማያስቆመው አስታውቀዋል።

በሌላ በኩል ከቤንሻንጉል ለተፈናቀሉ የአማራ ተወላጆች ድጋፍ ለመስጠት ከተለያዩ የኦሮሚያ ክልል የተሰባሰቡ 50 ወጣቶች በቅርቡ ወደ ባህርዳር እንደሚያመሩ የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

ቤንች ማጂ ዞን ቴፒ ከተማ ያለፉትን አራት ቀናት በሰላም አልቆየችም። በህዝቡ ውስጥ ለዘመናት ሲብላለ የከረመው ብሶትና ምሬት አደባባይ ወጥቶ በቁጣ የተገለጸበት ተቃውሞ ሲካሄድ ነበር የቆየው።

የኢሳት የመረጃ ምንጮች እንደገለጹት የአከባቢው ህዝብ ከሚደረስበት የአገዛዙ ግፍና በደል በተጓዳኝ ከአከባቢው ሀብት እንዳይጠቀም ተደርጎ በድህነት መማቀቁ ምሬቱን አባብሶታል።

ከአንድ ወር በፊት በጎጀብ የእርሻ ልማት ላይ የደርሰው ጥቃትም የአከባቢው ህዝብ ብሶቱን ወደ እርምጃ በመቀየር ተቃውሞውን አጠናክሮ መቀጠሉ የታየበት እንደሆነ የሚታወስ ነው።

ይሁንንና ይህን የህዝብ ተቃውሞ አቅጣጫ ለማሳትና በኢትዮጵያዋያን መሀል የእርስ በእርስ ግጭት መፍጠር ንመንግስታዊ ፖሊሲው በማድረግ በስልጣን ላይ የቆየው የህወሀት አገዛዝ በአካባቢው ነዋሪ በሆኑ የአማራ ተወላጆችና ንብረታቸው ላይ ጥቃት እንዲፈጸም ማድረጉ ነው የቴፒ ነዋሪዎች ለኢሳት ወኪል የገለጹት።

ሰሞኑን የተጀመረውን ተቃውሞ በሃይል ለማስቆም በአገዛዝዙ ታጣቂዎች የተወሰደው እርምጃ ውጤት ባለማምጣቱ ጉዳዩን ወደ እርስ በእርስ ግጭት እንዲቀየር መደረጉን ወኪላችን ካደረሰን መረጃ ለማወቅ ተችሏል።

በዚህ በቴፒ ነዋሪ በሆኑ የማራ ተወላጆች ላይ ጥቃት የተፈጸመ ሲሆን ንበርቶቻችው እንዲቀድም መደረጉም ታውቋል።

አገዛዙ በተለያዩ አካባቢዎች የአማራ ተወላጆች ላይ የጀመረውን አዲስ ዙር ጥቃት ተከትሎ በቤንች ማጂ ዞንም ተመሳሳይ ድርጊት መከሰቱ እንዳሳዘናቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል።

ለዘመናት ያመቅነውን ብሶት ለመተንፈስ ያገኝነበትን አጋጣሚ ሆን ብሎ በእርስ በእርስ ግጭት ለማበላሸት የተደረገ ከንቱ ሙከራ ነው ሲሉም ነዋሪዎች አገዛዙን አውግዘዋል።

እንዲህ ዓይነቱ ድርጊት የተጀመረውን የህዝብ ንቅናቄ ለማስቆም ቢሆንም እንድማይሳካ የገለጹት ነዋሪዎች ህዝቡ ሴራውን ተገንዝቦ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

በተያያዘ ዜና በአፋርና አማራ ክልል ወሎ ዳግም ግጭት ማገረሽቱን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

በሁለቱ ክልሎች ወሰን ላይ በየጊዜው የሚከሰተው ግጭት መፍትሄ ባለማግኘት የዘለቀ ሲሆን በእስከአሁን በርካታ ሰዎች ከሁለቱም ወገኖች መገደላቸው የሚታወስ ነው።

በመሬት ይዞታ ይገባኛል መነሻነት የተጀመረው ግጭት በአገዛዙ በኩል ሆን ተብሎ የሚካሄድ የማጋጨት ስትራቴጂ አካል መሆኑን የአፋር የሰብዓዊ መብቶች ድርጅት ለኢሳት ገልጿል።

ከትላንት ጀምሮ ቡርቃ ተብሎ በሚታወቅ በሁለቱ ክልሎች ወሰን ላይ በሚገኝ አከባቢ ሁለቱ ወገኖች ተፋጠው እንደሚገኙ የተገለጸ ሲሆን ደም አፋሳሽ ግጭት ሊከሰት እንደሚችል ስጋቱ በመገለጽ ላይ ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለም በቅርቡ ከቤንሻንጉል ክልል የተፈናቀሉትን የአማራ ተወላጆችን ለመርዳት ከተለያዩ የኦሮሚያ ክልል አከባቢዎች የተሰባሰቡ 50 የሚሆኑ የኦሮሞ ወጣቶች ወደባህርዳር ሊያቀኑ መሆኑ ታውቋል።

ወጣቶቹ ጣናም የእኛ ነው በሚል የጀመሩትን የትብብርና የወዳጅነት እንቅሳቅሴ በመቀጠል በችግር ላያ ላሉት የአማራ ተወላጆች አቅማቸው የፈቀደውን ለማድረግ በቅርቡ ወደባህርዳር እንደሚያመሩ የደረሰን መረጃ አመልክቷል።