(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 15/ 2010)በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዛሬ በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ፊትለፊት ታላቅ የተቃውሞ ሰልፍ አካሄዱ ።
በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲም ሰልፈኞቹን ላለማስተናገድ ቢሮውን ዝግ አድርጎ መዋሉም ታውቋል።
ሰላማዊ ሰልፈኞቹ በቅርቡ ገዛህኝ ገብረመስቀል /ነብሮ/ በቅጥረኛ ነብሰ ገዳይ መገደሉን እንዲሁም ከዘረፋ ጋር በተያያዘ ሌሎች አስር ኢትዮጵያውያን በደቡብ አፍሪካ መገዳላቸውን በመቃወም እንደሆነ ከአዘጋጆች ለማወቅ ተችሏል ።
ለተቃውሞ ከተለያዩ የደቡብ አፍሪካ ከተሞች የተሰባሰቡት ኢትዮጵያውያን ቁጥር በርካታ እንደሆን ነው ለማወቅ የተቻለው።
ፕሪቶሪያ ወደ ሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሲያመሩ በደቡብ አፍሪካ ፓሊስ በመታጀብ ነበር።
ሰላማዊ ሰልፉ እንዳይካሄድ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ የነበረው በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የሰላማዊ ሰልፈኞቹን ጥያቄና መልዕክት ላለመቀበል ቀድሞ ዝግ ለማድረግ በመወሰኑ ኤምባሲው ተዘግቶ እንደዋለ ለመርዳት ተችሏል።
በርካታ ኢትዮጵያውያን በተሳተፉበት በዚህ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ የሃይማኖት አባቶች ከፊት በማስቀደም የገዛህኝ ገብረመስቀልና እና ከዘረፋ ጋር በተያያዘ በደቡብ አፍሪካ የተገደሉትን ኢትዮጵያውያንን ፎቶ ግራፍ በመያዝ ከሰላማዊ ሰልፉ መነሻ 1 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር በመጓዝ ወደ ኤንባሲው አምርተዋል ።
በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ሰብሳቢ አቶ ታምሩ አበበ የተካሄደውን ሰላማዊ ሰልፍ አስመልክተው ለኢሳት እንደተናገሩት ዛሬ የተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ መነሻው የገዛህኝ ግድያ ቢሆንም የደቡብ አፍሪካና ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን በመኖራቸው ድምጻቸው ለዓለም እንዲሰማ በደቡብ አፍሪካ በዘራፊዎች የተገደሉ ኢትዮጵያውያንንም አስበናል ብለዋል።
አቶ ታምሩ አክለውም የኢትዮጵያ ኤምባሲ ታቃውሟችንን ላለመስማትና መልዕክታችንን ላለመቀበል በሩን ዘግቶ ቢሸሽም በደቡብ አፍሪካ ፓሊስ አማካይነት እንዲደርሳቸው አድርገናል ተቃውሟችንም ይቀጥላል ብለዋል ።
በዚህ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ከዚህ በፊት በሌሎች ጉዳዮች ላይ ተሳትፎ የሌላቸው ኢትዮጵያውያን መሳተፋቸው ታውቋል።
በሰልፉ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳተፈችው ወጣት ራህመት መሀመድ ለኢሳት እንደተናገረችው ገዛሕኝ ቢሞትም በርካታ ገዛህኞች ተፈጥረናል ብላለች ።
በደቡብ አፍሪካ ለነጻነት ይታገል የነበረው ገዛህኝ ገብረመስቀል ለጊዜው ማንነቱ ባልታወቀ ግለሰብ መገደሉና የግድያው ሁኔታም በግል መርማሪ ቡድን ምርመራው መቀጠሉ ታውቋል።
በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን ግድያው እንዲፈጸም የኢትዮጵያ ኤምባሲ ነብሰ ገዳይ ቀጥሯል በማለት የከሳሉ።