(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 9/2010)ትላንት የተገደሉት የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ስራ አስኪያጅ የዲፒ ከማራ ግድያ የአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንን ትኩረት መሳቡ ታወቀ።
ቁጥር አንድ ባለጸጋ የሆኑት የሚስተር አሊኮ ዳንጎቴ ንብረት የሆነው ዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ስራ አስኪያጅ ከሁለት ኢትዮጵያውያን ጋር የተገደሉት ትላንት ከቀትር በኋላ ምዕራብ ሸዋ ኢንጪኒ ላይ ነው።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2015 ስራ የጀመረው የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ዋና ስራ አስኪያጅ ሕንዳዊው ዲፒ ካማራ የተገደሉት ትላንት ረቡዕ ከቀትር በኋላ ነው።
ዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ከሚገኝበት ሙገር ከተማ ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ ከሁለት ኢትዮጵያውያን ጋር የተገደሉት ዲፒ ካማራ በአካባቢው ነዋሪዎች ዘንድ ተወዳጅ መሆናቸውም ተመልክቷል።
በዳንጎቴ ፋብሪካ ስራ አስኪያጅ ዲፒ ካማራና ስማቸው ባልተገለጸው ሁለቱ ኢትዮጵያውያን ላይ ግድያውን የፈጸሙት ግለሰቦች በሰለባዎቹ ላይ 15 ጥይት መተኮሳቸውን በአድአ በርጋ የኦሕዴድ ቢሮ ሃላፊ አቶ ድሪርሳ ታደሰ ለቢቢሲ ገልጸዋል። ስራ አስኪያጁ በ7 ጥይት መገደላቸው የተዘገበ ሲሆን አብረዋቸው የነበሩት ጸሃፊና ሹፌራቸውም ወዲያው ሕይወታቸው አልፏል።
ዳንጎቴ ሲምንቶ ፋብሪካ በኦሮሚያ ክልል ከተቀጣጠለው ሕዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተያያዘ ተሽከርካሪዎቹና የተለያዩ የፋብሪካው ማምረቻ እቃዎች እንደተቃጠሉበት ይታወሳል።
ከግርግሩ በኋላ በፋብሪካ ውስጥ የአካባቢውን ነዋሪዎች ይበልጥ በማሳተፍም የሕዝቡን ቅሬታ እየገፈፈ መምጣቱም ተመልክቷል።
በተለይም በዚህ አመት መጀመሪያ መስከረም ላይ የፋብሪካው ስራ አስኪያጅ ሟቹ ዲፒ ካማራ ቁጥራቸው 1 ሺ 500 ከሚሆኑ የሙገር ከተማ ነዋሪዎች ጋር ያደረጉት ውይይት ይበልጥ መግባባትን የፈጠረ እንደነበርም ተመልክቷል።
በዚህም የአካባቢው ነዋሪ ኦቦ ገለታ እያለ እንደሚጠራቸውና በአባትነት እንደሚመለከታቸው ዘገባዎች አመልክተዋል።
የአፍሪካው ቁጥር አንድ ሐብታም የናይጄሪያው ተወላጅ አሊኮ ዳንጎቴ ንብረት የሆነው ዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ በኢትዮጵያ ስራ የጀመረው እንደአውሮፓውያኑ በ2015 ነው።