(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 8/2010)ሰሜን ኮሪያ ከጎረቤቷ ደቡብ ኮሪያ ልታደርግ የነበረውን ውይይት ሰረዘች።
ሰሜን ኮሪያ ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትረምፕ ጋር ለመገናኘት የያዝኩትንም እቅድ ልሰርዝ እችላለሁ ማለቷም ተሰምቷል።
ሰሜን ኮሪያ አሜሪካ በኒዩክለር መሳሪያዬ ላይ ያላት አቋም አስገዳጅ ይመስላል ይህ ተከትሎም ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ጋር ላልገናኝ እችላለሁ ብላለች።
ከወር በፊት ነበር የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆን ኡን ከ 63 አመታት በኋላ የመጀመሪያ ነው የተባለና ታሪካዊ የሆነውን የደቡብ ኮርያ ጉብኝት ያደረጉት።
ይህም የሁለቱ ሃገራት ግንኙነት ደግሞ የቆየውን የጠብ ግድግዳ ያፈረሰ ነው በማለት ሙገሳን ከማግኘቱም በላይ የአለምን ቀልብ መሳብ የቻለ ክስተት ነበር።
ዛሬ ላይ ተስፋ የተጣለበት የሁለቱ ሃገራት ግንኙነት ጥላ አጥልቶበታል።
ይህም የሆነው የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ከጎረቤቴ ደቡብ ኮሪያ ጋር ላደርግ የነበረውን ውይይት ሰርዣለሁ ማለታቸውን ተከትሎ ነው።
በዚህ ሳያበቁ ኪምጆንግ ኡን ከአሜሪካ ጋር በሰኔ 12 በሲንጋፖር የያስኩትን ቀጠሮ ልሰርዝ እችላለሁ ብለዋል።
ኪም ጆንግ ኡን ከደቡብ ኮሪያ ጋር ለነበረው ውይይት መሰረዝ ምክንያት አድርገው ያስቀመጡትም አሜሪካ በተደጋጋሚ የኒዩክለር መሳሪያዬን በተመለከተ ያላት አቋም አስገዳጅ ስለሚመስል ነው።
በደቡብ ኮሪያ በኩልም ጫና ለማሳደር ሞክራለች ይህም አላስደሰተኝም ማለታቸውን ነው ቢቢሲ የዘገበው።
በቁጣ የተሞላ ነው በተባለው በዚህ የሰሜን ኮሪያ መግለጫ አሜሪካ በኮሪያ ባህረ ሰላጤ ላይ ያላትን አቋም ማጤን አለባት ካለዛ የጦር መሳሪያን በተመለከተ ውይይት አላደርግም የሚል ሃሳብም ተነስቷል።
የኮሪያን ቀጠና ከኒዩክለር ነጻ ለማድረግ ውይይት የጀመርነው ፍላጎት ስላለን እንጂ በማንም አስገዳጅነት አይደለም ብላለች ሰሜን ኮሪያ።
ሰሜን ኮሪያ ይህንን ትበል እንጂ አሜሪካ በአጸፋው ሰሜን ኮሪያ ለመወያየት ፍላጎት እስካለት ድረስ በኔ በኩል ዝግጁ ነኝ ስትል ምላሽ ሰጥታለች።