(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 7/2010)የልብ ቀዶ ሕክምና ባለሙያው ዶክተር ፍቅሩ ማሩ ከእስር ተለቀቁ።
የ66 አመት እድሜ ያላቸው ስዊዲናዊውው ትውልደ ኢትዮጵያዊ ዶክተር ፍቅሩ ማሩ ከ5 አመታት እስር በኋላ ከቃሊቲ ወህኒ ቤት ወጥተዋል።
በቅሊንጦ ቃጠሎ በግድያ ወንጀል ተከሰው ከነበሩት 38 ሰዎች ክሳቸው እንዲነሳ ሲወሰን አራቱ በነጻ ተለቀው ቀሪዎቹ ደግሞ የፍርድ ሂደታቸው እንዲቀጥል መባሉ ይታወሳል።
በእነመቶ አለቃ ማስረሻ ስጤ መዝገብ አግባው ሰጠኝን ጨምሮ 62 ሰዎች በይቅርታ ከእስር ተለቀዋል።
ዶክተር ፍቅሩ ማሩ በመጀመሪያ የታሰሩት የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል በሚል ሰበብ ነው።
የልብ ሕክምና ልዩ ሐኪም ሆነው የአዲስ የልብ ሕክምና ሆስፒታልን በመክፈት በርካታ ኢትዮጵያዊንን የረዱት ዶክተር ፍቅሩ ማሩ ያለቀረጥ የሕክምና መሳሪያ አስገብተዋል በሚል በሙስና ተወንጅለው ከ5 አመታት በላይ ታስረዋል።
የሕክምና መሳሪያ ከቀረጥ ነጻ ወደ ኢትዮጵያ አስገብተዋል በሚል የተፈረደባቸውና በኋላም በጠቅላይ ርድ ቤት በነጻ የተሰናበቱት ዶክተር ፍቅሩ ማሩ ከቂሊንጦ የእስር ቤት ቃጠሎ ጋር በተያያዘ ፍርድ ቤት ሲመላለሱ ቆይተዋል።
ዶክተር ፍቅሩ ማሩ በቂሊንጦ ቃጠሎ የሽብር ወንጀል ፈጽመዋል፥ የግንቦት ሰባትና የኦነግ ቡድን በእስር ቤት አደራጅተዋል በሚልም ከሌሎች 38 ሰዎች ጋር ተወንጅለውም ጉዳይ በክስ ሂደት ላይ ነበሩ።
ከእስር ቤት እየተመላለሱ ሕክምና ሲሰጡ ከቆዩ በኋላ እንደገና በመታገዳቸው ከ20 በላይ ሕሙማን እንደሞቱ ለቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ፍትህ እንዲሰጧቸው ጠይቀው ሰሚ አላገኙም ነበር።
ይህም ሁሉ ሆኖ ግን በሕዝብ ትግል እና ጫና የደረሰበት የኢትዮጵያው አገዛዝ በመጨረሸ ዶክተር ፍቅሩ ማሩን ጨምሮ እስረኞችን ለመልቀቅ ተገዷል ።
ዶክተር ፍቅሩ ማሩ ከእስር እንዲለቀቁ የስዊድን መንግስትም የራሱን ጠረት ሲያደርግ ቆይቷል።
ከፖለቲካ ጋር በተያያዘ የታሰሩት ጋዜጠኞችና ታዋቂ ሰዎች አብዛኞቹ ከእስር ቢለቀቁም አሁንም በሐገሪቱ በሺህዎች የሚቆጠሩ እስረኞች መኖራቸው ይነገራል።