(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 3/2010) አሜሪካ በኢራን ባለሃብቶችና ግለሰቦች ላይ ማዕቀብ ጣለች።
ይህን ተከትሎም ኢራን ስምምነቱ በዚህ መልኩ የሚፈርስ ከሆነ ዩራኒየም የማበልጸጌን ስራ ለመጀመር ተዘጋጅቻለሁ ስትል ምላሿን ሰታለች።
በሌላ በኩል እስራኤል ኢራን በሶሪያ ባላት የጦር ሰፈር ላይ ያደረሰችውን ጥቃት ተከትሎ በአካባቢው ውጥረት መንገሱ ተሰምቷል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የ2015ቱን የኢራንና የሃያላኑ ሃገራትን የዩራኒየም ማበልጸግ ስምምነት ማፍረስን ተከትሎ የተለያዩ ውዝግቦች በመነሳት ላይ ናቸው።
የፕሬዝዳንት ትራምፕን ውሳኔ ተከትሎ በ2 ቀናት ውስጥም አሜሪካ በኢራን ባለሃብቶች ላይ ማእቀብ መጣሉዋ ነው የተሰማው።
እንደ ቢቢሲ ዘገባ ከሆነም የአሜሪካ ግምዣ ቤት በስድስት የኢራን ባለሃብቶችና በ3 ኩባንያዎች ላይ እንዳይንቀሳቀሱ እገዳ ጥሏል።
የግምዣ ቤቱ ጸሃፊ ሙንችሂን እንዳሉት እነዚህ ኢራናውያን ግለሰቦች ሚሊዮን ዶላሮችን ለኢራን አብዮታዊ ዘብ ፈሰስ ያደርጋሉ ከወታደራዊ ባለስልጣናቱም ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ደርሰንበታል ነው ያሉት።
አብዮታዊ ዘቡ በሃገሪቱ ሃይማኖታዊ መሪ አህያቶላ ካሚኒ የሚመራ ሲሆን በሃገሪቱ ቁልፍ የሚባሉ ቦታዎች ላይ የሀገሪቱን ጦር ሰራዊት ያግዛሉ ያለው የቢቢሲ ዘገባ ይሁን እንጂ ታጣቂ ቡድኑ በአሜሪካ ዘንድ እምነት የሚጣልበት አለመሆኑን ነው ለማወቅ የተቻለው።
ይህ የአሜሪካ ርምጃም ቡድኑን ለማጠናከር የሚደረገውን እንቅስቃሴ ለመግታት ያለመ ነው ተብሏል።
የኢራን መንፈሳዊ መሪም አያቶላህ ካሚኒ ይህ ትልቅ ስህተት ነው ሲሉ ምላሻቸውን ሰጥተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም እስራኤል ሶሪያ በሚገኘው የኢራን የጦር ሰፈር ላይ የሚሳኤል ጥቃት መሰንዘሯ ተሰምቷል።
ኢራን በጎላን ኮረብታዎቼ ላይ 20 የሚሳኤል ሙከራን አደርጋለች 16ቱ ቢከሽፉም 4 ቱ ግን በግዛቴ ለይ አርፈዋል ለዛም የአጽፋ ምላሽ የሰጠሁት ብላለች እስራኤል።
የእስራኤል ጥቃቱ ኢላማ ያደረገው የኢራንን የጦር መሳሪያ ክምችት ያለበትን ስፍራ ሲሆን ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል መባሉንም ዘገባው አመልክቷል።
ሩሲያ ጀርመንና ፈረንሳይ ሁለቱም ሃገራት አርፈው እንዲቀመጡ ሲያስጠነቅቁ አሜሪካ በበኩሏ በጉዳዩ ኢራን ሃለፊነት መውሰድ አለባት ማለቷ ተሰምቷል።