ብአዴን በባህርዳር ከተማ እያደረገ ባለው ስብሰባ ላይ የድርጅቱ አመራሮች እርስ በርስ እየተወዛገቡ ነው
(ኢሳት ዜና ግንቦት 01 ቀን 2010 ዓ/ም) ሚያዝያ 27 የተጀመረው የብአዴን ስብሰባ በውዝግቦች ታጅቦ እንደቀጠለ መሆኑን ምንጮች ገለጹ። ከዞን አመራሮች፣ የብአዴን ከፍተኛና የበላይ ሃላፊዎች እንዲሁም ከአዲስ አበባና ሌሎች አካባቢዎች የተጠሩ የብአዴን አመራሮች በተገኙበት ስብሰባ ላይ የቀረቡት አጀንዳዎች የውዝግቡ መነሻ ሆነዋል። አጀንዳዎቹ ሲቀርቡ አመራሮች ከዚህ በፊት እንደነበረው ሳይሆን በስሜትና አልፎ አልፎም በመዘላለፍ እርስ በርስ ይተቻቹ እንደነበር የሚገልጹት ምንጮች፣ በተለይ አዳዲስ የዞን አመራሮች ስብሰባውን የሚመራውን የድርጀቱን ሊቀመንበር አቶ ደመቀ መኮንን በጠንካራ ቃላት ሲናገሩት እንደነበር ምንጮች ገልጸዋል።
አቶ ደመቀ የሚፈልገው ሰው ሃሳብ ሲሰጥ እንደማያስቆም፣ እርሱና ባልደረቦቹ የማይደግፉት ሃሳብ ሲቀርብ ደግሞ ተናጋሪውን ማቋረጡ ያበሳጫው ተሰብሳቢዎች፣ “ደመቀ ስነስርዓት አድርግ፣ አቁም! አርፈህ ተቀመጥ!” በማለት ተናግረውታል።
አካሄዱ ያልጣመው አቶ በረከት ስምዖን በበኩሉ፣ በስሜት ውስጥ ሆኖና ጠንካራ ቃላትን በመጠቀም “ ቃል በቃልና በሃሳብ ማሸነፍ ሲቻል ለምን ጭቅጭቅ ይነሳል” በማለት መድረኩን ለማረጋጋት ቢሞክርም፣ በአብዛኛው ወጣት አመራሮች ዘንድ በካህዲነት በመፈረጁ እንደ ወትሮው የሚሰማው አላገኘም።
በብአዴን ማአከላዊ ኮሚቴ ጽ/ቤት የገጠር ፖለቲካና አደረጃጀት ዘርፍ ሀላፊ የሆኑት አቶ ጌታቸው ጀንበር “የአስተሳሰብ ወይም የአመለካከት ግንባታ ላይ ትኩረት ያደረገ ሰፊ ግምገማ እየተካሄደ መሆኑን ቢገልጹም፣ የአስተሳሰብ ግንባታው ግን “አዲስ መንገድ እንከተል” በሚሉት ወጣት አመራሮችና ነባሩን የአብዮታዊ ዲሞክራሲ መንገድ እንደያዝን መጓዝ አለብን በሚሉት በእነ በረከት መካከል ሰፊ የሃሳብ ልዩነት ተፈጥሯል።
በርካታ ወጣት አመራሮች የአማራ ህዝብ ባለፉት 27 አመታት ከስርዓቱ ያገኘው ነገር እንደሌለ እና ይህን የተዛባ አንድን ወገን ተጠቃሚ ያደረገ አሰራር መቀየስ እንደሚገባ ሃሳብ ሰንዝረዋል።
በበረከት ስምኦንና በአቶ ደመቀ መኮንን መካከልም ከዚህ በፊት የነበረው አይነት ወዳጅነት የሌለ መሆኑን የሚገልጹት ምንጮች፣ አቶ ደመቀ አቶ በረከት በጠ/ሚኒስትርነት ምርጫ ወቅት ከህወሃት ጋር በመወገን ይዞት የነበረውን አቋም በመንቀፍ አስተያየት ሰጥቷል። አቶ በረከት አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ጠ/ሚኒስትር ሆኖ እንዲመረጥ ከህወሃት ጋር በመሆን ይሰራ ነበር የሚለው በወጣት የአብዴን አመራሮች ዘነድ ቅሬታ አሳድሯል።
አቶ በረከት የዶ/ር አብይን አካሄድ ከሚቃወሙት ነባር አመራሮች መካከል ግንባር ቀደሙ ነው። ብአዴን ለዲሱ ጠ/ሚኒስትር ድጋፍ እንዳይሰጥ ለማሳመን በረከት ጥረት እያደረገ መሆኑን ምንጮች አክለው ገልጸዋል።