በሻኪሶና አካባቢዋ የሚካሄደውን ተቃውሞ ለማፈን ተጨማሪ የአጋዚ ወታደሮች ወደ ስፍራው ተላኩ

በሻኪሶና አካባቢዋ የሚካሄደውን ተቃውሞ ለማፈን ተጨማሪ የአጋዚ ወታደሮች ወደ ስፍራው ተላኩ
(ኢሳት ዜና ግንቦት 01 ቀን 2010 ዓ/ም) ትናንት ደም አፋሳሽ ሆኖ ሲካሄድ የነበረውን የሻኪሶ ዞን ተቃውሞ ተከትሎ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የአጋዚ ወታደሮች ወደ ስፍራው በማቅናት ተቃውሞውን በሃይል ለማፈን ሙከራ እያደረጉ ነው።
ዛሬ ረቡዕ ከሻኪሶ እስከ ደቡብ ክልል ድንበር ቦሬ ድረስ የመከላከያ ሰራዊት የተሰማራ ሲሆን፣ አካባቢው ከፍተኛ ጦር የሚካሄድበት ቦታ ይመስላል ሲሉ ነዋሪዎች ይናገራሉ።
ምንም እንኳ ወታደሮች የተዘጉ መንገዶችን እየጠረጉ ለመክፈትና የትራንስፖርት አገልግሎትም ለማስጀመር ቢችሉም፣ ህዝቡ ግን ቤቱ በመቀመጥና የንግድ ድርጅቶቹን በመዝጋት የቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማ በማድረግ ላይ መሆኑን ነዋሪዎች ገልጸዋል።
ትናንት በነበረው ተቃውሞ ከ1 እስከ 4 የሚጠጉ ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ይናገራሉ።
ህዝቡ ለሚያቀርበው ጥያቄ የመንግስት ባለስልጣናት እስካሁን አጥጋቢ ምላሽ አልሰጡም። የህዝቡ ጥያቄ ባለመመለሱም ትግሉ እንደሚቀጥል ነዋሪዎች ይገልጻሉ።
ስቱዲዩ ከገባን በኋላ የማዕድን፣ ነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር የሚድሮክ ጎልድ የለገደምቢ የወርቅ ማዕድን ማውጣት ፍቃድ ከዛሬ ጀምሮ መታገዱን ገልጿል