አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እንዲፈታ በማህበራዊ ሚዲያ የተካሄደው ዘመቻ የተሳካ እንደነበር ወ/ት እየሩሳሌም ተስፋው ገለጸች

አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እንዲፈታ በማህበራዊ ሚዲያ የተካሄደው ዘመቻ የተሳካ እንደነበር ወ/ት እየሩሳሌም ተስፋው ገለጸች
(ኢሳት ዜና ግንቦት 01 ቀን 2010 ዓ/ም) በቅርቡ በሽብር ወንጀል ተከሳ የፍርድ ጊዜዋን ጨርሳ ከእስር የተፈታችው ወጣት እየሩሳሌም ተስፋው ለኢሳት እንደገለጸችው አቶ አንዳርጋቸው ከእስር እንዲፈታ ሰደረግ የነበረው የ3 ቀናት ዘመቻ ዛሬ ረቡዕ የሚጠናቀቅ ሲሆን፣ እስካሁን በነበረው ዘመቻ በአብዛኛው ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች ዘመቻውን ተቀላቅለው ድምጻቸውን በማሰማታቸው የተሳካ ዘመቻ ተደርጓል ብላ እንደምታስብ ተናግራለች።
“ዘመቻው ውጤት የሚያመጣ ይመስልሻል?” የሚል ጥያቄ የቀረበላት እየሩሳሌም፣ “በዚህ ዘመቻ አንዳርጋቸው ከተፈታ ጥሩ ነው፣ ካልሆነ ግን ወደ ሚቀጥለው እንቅስቃሴ እንናመራለን” ብላለች።
“በቅርቡ ከእስር ቤት ተፈተሽ ሳታርፊ አሁን ደግሞ አንዳርጋቸው እንዲፈታ ዘመቻ የጀመርሽበት ምክንያት ምንድነው?” ተብሎ ለቀረበላት ጥያቄ ደግሞ “ የአንዳርጋቸው ጉዳይ እስር ቤት ከመግባቴ በፊት ሁሉ ያንገበግበኝ ነበር፣ እስር ቤት እያለሁም ስለ እሱ ጽሁፍ ለመላክ ሞክሬ ነበር፣ ስወጣም የተለዬ ነገር የለም፤ አንዳርጋቸው ለእኛ ብዙ ነገር ሆኗል፣ ብዙ ስቃይ ከፍሏል” በማለት ምክንያቶቿን አብራርታለች።