በሶማሊ ክልል ጠንካራ ተቃውሞ ሲካሄድ ዋለ
(ኢሳት ዜና ሚያዝያ 30 ቀን 2010 ዓ/ም) የአብዲ ኢሌን ፍጹማዊ አገዛዝ በመቃወም በሶማሊ ክልል የሚካሄደው ተቃውሞ አድማሱን እያሰፋ በመምጣት ላይ ነው። በዛሬው እለት ከዚህ በፊት ተቃውሞ ባልተካሄደባቸው ቦታዎች ጠንካራ ተቃውሞ ሲካሄድ ውሎአል። የአብዲ ኢሌ ተጣቂዎች ተቃውሞአቸውን በሚገልጹ ዜጎች ላይ በወሰዱት እርምጃም ሰዎች ተገድለዋል። ቶጎ ወጀሌንና ጂግጂጋን ከመሃል አገር ጋር የሚያገናኘው መንገድም ተዘግቷል።
በጅግጅጋ ዞን በቶጎ ወጀሌ በሚካሄደው ተቃውሞ የአብዲ ኢሌ ልዩ ሚሊሺያዎች በወሰዱት እርምጃ እስካሁን በትንሹ 3 ሰዎች ሲገደሉ ከ20 በላይ ደግሞ ቆስለዋል። ተቃውሞው በአይሻኣ፣ በሃሮረይስ፣ በቢኪ እና በጎብየር ከተሞች ተካሂዷል።
ህዝቡ አብዲ ኢሌ ስልጣኑን ለቆ ለፍርድ እንዲቀርብ ጥያቄ እያቀረበ ሲሆን፣ የአብዲ ኢሌ አገዛዝ ተቃውሞውን በሃይል ለማፈን ጥረት እያደረገ ነው።
የሶማሊ ክልል ፕሬዚዳንት አብዲ አሌ በእርሱ ላይ የሚካሄደውን ተቃውሞ የአቶ ለማ መገርሳና የዶ/ር አብይ አህመድ ቡድን ከጀርባ ሆነው እንደሚመሩት እየገለጸ ነው። በክልሉ ውስጥ የዶ/ር አብይ ፎቶ ግራፍ እንዲወርድ ወይም እንዲቀቀድ መደረጉን የሚገልጹት ምንጮች፣አቶ አብዲ” ኦሮምያ ክልል ሰላማችን የማይሰጠን ከሆነ እኛም ለኦሮምያ ሰላም አንሰጥም” በማለት በሞያሌና ሌሎችም አካባቢዎች ተቃውሞዎችን እያስነሳና ለማስነሳት እየሞከረ ነው ብለዋል።
የህወሃት ድጋፍ ያለው አቶ አብዲ ኢሌ አሁን አሁን የጦር ጄኔራሎች በበቂ ሁኔታ ድጋፍ እየሰጡኝ አይደለም የሚል ፍርሃት እያደረበት መጥቷል። በዚህም የተነሳ ከዋናዋ ሶማሊያ ጋር የጠበቀ ቁርኝት በመፍጠር እንደ መጨረሻ አማራጭ ኦጋዴንን ገንጥሎ ወደ ሶማሊያ እንደሚቀላቅላት እየዛተ መሆኑን ምንጮች አክለው ገልጸዋል።
የዛሬውን ተቃውሞ በተመለከተ ኢሳት ያነጋገራቸው ሻለቃ አሊ ሰምሬ ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ የእርስበርስ ግጭት ሊነሳ ይችላል ይላሉ።