በቂሊንጦ ቃጠሎ ሰበብ ከተከሰሱት የህሊና እስረኞች መካከል ብዙዎቹ በመደበኛ ወንጀል እንዲካላከሉ ተበየነ

በቂሊንጦ ቃጠሎ ሰበብ ከተከሰሱት የህሊና እስረኞች መካከል ብዙዎቹ በመደበኛ ወንጀል እንዲካላከሉ ተበየነ
(ኢሳት ዜና ሚያዝያ 30 ቀን 2010 ዓ/ም) የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት በቂሊንጦ ቃጠሎ ሰበብ ታስረው አሁንም ድረስ ጉዳያቸውን በፍርድ እየታየ ከሚገኙት መካከል መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጠኝ፣ ዶክተር ፍቅሩ ማሩን፣ አግባው ሰጠኝን፣ ወልዴ ሞቱማን፣ ሚስባህ ከድርን፣ ፍቅረማርያም አስማማውን፣ ደረጀ መርጋንና፣ ከበደ ጨመዳን፣ ጨምሮ 28 ተከሳሾችን አመፅ በማደራጀት፣ በመምራትና በመሳተፍ በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ አንቀፅ 464/2/ሀ፣ ለ፣ 461/ሀ እና 494 /2 ስር እንዲከላከሉ በይኖባቸዋል።
ከተከሳሾች መካከል ጌታቸር እሼቴ፣ ቶፊቅ ሽኩር፣ ሸምሱ ሰኢድ እና ፍፁም ጌታቸው በተገደሉት ሰዎች ነፍስ እንዲከላከሉ ሲበየንባቸው፣ አብዱሉሂ አልዩ፣ እስማኤል በቀለ፣ ቃሲም ገንቦ፣ አንጋው ተገኘ፣ ሰይፈ ግርማ፣ ዲንሳ ፉፉ፣ ናስር ደጉና ናኦል ሻሜሮ በነፃ እንዲሰናበቱ ተበይኗል።
34ኛ ተከሳሽ ፍጹም ጌታቸው “በቃጠሎው የተገደለውኮ አብሮ አደጌ፣ የሰፈሬ ልጅ፣ ጓደኛዬ ነው። አባቴ የእሱን ሞት ሰምቶ በልብ ድካም ነው የሞተው” ብሎ ተናግሯል።
ተከሳሾች የተሰጠውን ብይን እንደማይቀበሉት ገልጸዋል። ወላጆች በውሳኔው ተባስጭተው ተቃውሞቸውን በለቅሶ ሲቃወሙ የፌደራል ፖሊሶች በጠመንጃ በማስፈራራት ችሎቱን በትነውታል።