ሳኡዲ አረቢያ-ከሶማሊያ የቀንድ ከብት ወደ ሀገሯ እንዳይገባ የጣለችውን እግድ ልታነሳ መሆኗን አስታወቀች።

ሳኡዲ አረቢያ-ከሶማሊያ የቀንድ ከብት ወደ ሀገሯ እንዳይገባ የጣለችውን እግድ ልታነሳ መሆኗን አስታወቀች።
(ኢሳት ዜና ሚያዝያ 30 ቀን 2010 ዓ/ም) የመካከለኛዋ ምሥራቅ ሀገር “ከብቶቹ በሽታ ተገኝቶባቸዋል” በሚል ምክንያት ከሶማሊያ የቀንድ ከብት ማስገባት ያቆመችው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2016 ነው።
ሳኡዲ አረቢያ የበርበራ፣ የቦሳሶ፣ የሞቃዲሾ እና የሌሎች ከተሞች ወደቦችን በመጠቀም 80 በመቶ የሚሆኑትን የሶማሊያ ቀንድ ከብቶች ወደ ሀገሯ ስታስገባ ወይም ኢምፖርት ስታደርግ ቆይታለች።
በአሁኑ ወቅት ሶማሊያ-ከመካከለኛዋ ምሥራቅ ሀገር ጋር መልካም ግንኙነት በመፍጠሯ ፣ሪያድ ክልከላውን በማንሳት ከሞቃዲሾ ጋር መሥራት ትጀምራለች።
የዓለማቀፉ ግጭት አጥኝ ቡድን የአፍሪካ ቀንድ ፕሮጀክት ዳይሬክተር ረሽድ አብዲ ለሶማሊያ የቢቢሲ ወኪል ለሜሪ ሀርፐር እንደተናገሩት፣ ሶማሊያ ለመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት የኃይል አሰላለፍ የቼስ ቦርድ መጫዎቻ እየሆነች ነው።
በአንድ በኩል ኳታር እና ቱርክ፣ በሌላ በኩል ሳኡዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኢምሬት፣ እና አጋሮቻቸው።
“እነዚህ ተቀናቃኞች በአፍሪካ ዙሪያ ተመሣሳይ ውጥረትና ሽኩቻ ውስጥ እንደሚገቡ ምንም የሚያጠራጥር አይደለም”ሲሉም ዳይሬክተሩ ያክላሉ።
ሶማሊያ ደግሞ በተለዬ መልኩ ለባህረ ሰላጤው ሀገራት ካላት ቅርበት እና ከክልሉ ጋር ከነበራት ረዥም ታሪካዊ ግንኙነት አንጻር ለዚህ ዓይነት ሽኩቻ የተጋለጠች መሆኗን ሚስተር ረሽድ አስረድተዋል።