ዶክተር አብይ አህመድ በመጪው ነሃሴ አሜሪካን ይጎበኛሉ ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 30/2010)  ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በመጪው ነሃሴ አሜሪካን እንደሚጎበኙ ከዲፕሎማቲክ ምንጮች የተገኘ መረጃ አመለከተ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ አምባሳደር ቲቦር ናዢ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር እንዲሆኑ  መታጨታቸው ተነግሯል።

በኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው ያገለገሉት ቲቦር ናዥ የአፍሪካ ጉዳዮች ሃላፊ እንዲሆኑ በአሜሪካ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት  ወይንም ሴኔት በቅርቡ ይጸድቅላቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

አዲሱ የአፍሪካ ጉዳዮች ሃላፊ ከተሾሙ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በመጪው ነሃሴ አሜሪካን እንደሚጎበኙ ከዲፕሎማቲክ ምንጮች የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የዲፕሎማቲክ ምንጮች እንዳሉት በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ሃላፊ መሾሙና የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የአሜሪካ ጉዞ በተቀራራቢ ግዜ ውስጥ መሆን የተለየ ግኑኝነት የለውም።

ሙሉ ስልጣን ያለው ሃላፊ በተሾመ  ማግስት  የሚደረግ ጉዞ ግን  ተጠባባቂ ሃላፊ እያለ ከሚደረግ ጉዞ የተሻለ መሆኑን  ግን እነዚሁ የዲፕሎማቲክ ምንጮች ይናገራሉ።

በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዋና ሃላፊ በመሆን የታጩት ሚስተር ቲቦር ናዥ  ተጠባባቂ ረዳት ሚኒስትር የሆኑትን አምባሳደር ዶናልድ ያማማቶን እንደሚተኩ ነው የተነገረው።

አሁን የሚለቁት አምባሳደር ያማማቶም ሆኑ አዲስ የሚመጡት አምባሳደር ቲቦር ናዥ  ሁለቱም በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር በመሆን አገልግለዋል።

አምባሳደሩ ስለመሾማቸው በኋይት ሃውስ በኩል እስካአሁን ባይገለጽም የፕሬዝዳንት  ዶናልድ ትራምፕ ዕጩ ሚስተር ቲቦር ናዥ መሆናቸውን ምንጮች ገልጸዋል።

ሚስስ ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልግ አምና በመጋቢት  2017 ስልጣናቸውን ከለቀቁ ጀምሮ የአፍሪካ ጉዳዮች የሃላፊነት ቦታ ከአንድ አመት በላይ ሰው ሳይሾምበት በተጠባባቂ ተይዞ ቆይቷል።

በትውልደ ሃንጋሪያዊ የሆኑት እና በልጅነታቸው በስደተኝነት አሜሪካ የገቡት የ 68 አመቱ ቲቦር ናዥ  እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ1999 እስከ 2002 በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ሆነው አገልግለዋል።

በአሜሪካ የውጭ  ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ሃላፊነት ቦታ በአፍሪካ ጉዳይ ወሳኝ ስፍራ ስለመሆኑም ይገለጻል።

በደርግ ውድቀት ዋዜማ በደርግ እና በአማጽያኑ መካከል በለንደን የተካሄደውን ድርድር የመሩት በወቅቱ  የአፍሪካ ጉዳዮች ሃላፊ የነበሩት አምባሰደር ህርማን ኮኾን እንደነበሩም ይታውሳል።

የቀድሞው የሲ አይ ኤ ዳይሬክተር ማይክ ፖምፒዮ በቅርቡ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው መሾማቸው ይታወሳል።