(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 30/2010) በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ሕገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር በስፋት እየተካሄደ መሆኑን ሃገሪቱን እየገዛ ያለው ወታደራዊ እዝ/ኮማንድ ፖስት/አስታወቀ።
በተጠናቀቀው ሚያዚያ ብቻ ከ2 መቶ በላይ ልዩ ልዩ የጦር መሳሪያዎች በድብቅ ሲዘዋወሩ መያዙን ኮማንድ ፖስቱ ገልጿል።
ኮማንድ ፖስቱ በሞያሌ ከተማ የተከሰተውን ግጭትና በዚሁ ሰበብም በርካታ ሰዎች መሞታቸውን አስታውቋል።
በኢትዮጵያ የተደነገገው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚያስፈጽመው ወታደራዊ እዝ/ኮማንድ ፖስት/በሞያሌ ግጭት ተፈጥሮ በርካታ ሰዎች መሞታቸውንና መቁሰላቸውን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ይህም ሆኖ የሞቱትንና የቆሰሉትን ሰዎች ቁጥር ከመግለጽ ተቆጥቧል።
ቢቢሲ አማርኛ ከሞያሌና ያቤሎሆስፒታሎች ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው በግጭቱ ከ10 ያላነሱ ሰዎች ተገድለዋል።
በሞያሌ ከትላንት በስቲያ ሚያዚያ 28/2010 በሁለት አቅጣጫ ግጭት እንደነበር ከመግለጽ ውጭም ውጊያው በማንና በማን መካከል እንደተካሄደም ያለው ነገር የለም።
የአካባቢው ምንጮች እንደሚሉት ግን ግጭቱ በሶማሌ ልዩ ሃይልና በኦሮሚያ ታጣቂዎች መካከል የተካሄደ ነበር።
ኮማንድ ፖስቱ በመግለጫው እንዳለው በኢትዮጵያ ሕገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር በእጅጉ እየተስፋፋ መጥቷል።
እንደ መግለጫው በተጠናቀቀው ሚያዚያ ወር ብቻ 142 ክላሽ፣88 ሽጉጦችና 17 የነፍስ ወከፍ መሳሪያዎች ከበርካታ ጥይቶች ጋር እንዲሁም 11 የእጅ ቦምቦች ሊያዙ ችለዋል።
ኮማንድ ፖስቱ የሞያሌ አካባቢን ጨምሮ በጦር መሳሪያ ታግዞ አገዛዙን እየተፋለመ ያለውን ሕዝብ ትጥቅ እያስፈታ ይገኛል።
ይህም ዘመቻ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያለው።
ከትላንት በስቲያ ጀምሮ በሞያሌ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች ወደ ኬንያ እየተሰደዱ መሆናቸውን ያገኘነው መራጃ ያመለክታል።