በአባይ ግድብ ዙሪያ በአዲስ አበባ የመከረው ስብሰባ ያለውጤት ተጠናቀቀ

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 29/2010) በአባይ ግድብ ጉዳይ ላይ በአዲስ አበባ የመከሩት የ3ቱ ሀገራት የመስኖ ሚኒስትሮች ስብሰባ ያለውጤት ተጠናቀቀ።

የኢትዮጵያ፣የግብጽና የሱዳን ሚኒስትሮች በቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ ምክክር ቢያደርጉም ስብሰባው ያለውጤት ተጠናቋል።

ስብሰባው ያለውጤት ቢጠናቀቅም ከአንድ ሳምንት በኋላ እያንዳንዱ ሀገር 3 ሚኒስትሮች የሚወከሉበት 9 አባላት ያሉት ውይይት እንደገና ለማካሄድ ቀጠሮ ይዘዋል።

በአባይ ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያና የሱዳን አቋም ተመሳሳይ እንደሆነ ይነገራል።

በግብጽ በኩል ግን የግድቡ ግንባታ በአባይ ላይ ያለኝን የውሃ ጥቅም ይነካል የሚል ስጋት መኖሩ ነው የሚነገረው።

የሶስቱ ሀገራት የውሃና መስኖ ሚኒስትሮች ባለፈው ሚያዚያ በሱዳን ካርቱም ቢመክሩም አሁንም በግብጽ አለመስማማት ስብሰባው ያለውጤት ተጠናቆ ነበር።

አሁን ደግሞ ላለፉት 2 ቀናት በአዲስ አበባ የተካሄደው የሶስቱ ሚኒስትሮች ስብሰባ ያለውጤት ተጠናቋል።

የኢትዮጵያ የውሃና የመስኖ ሚኒስትሮች አቶ ስለሺ በቀለ የሱዳኑ አቻቸው ሞታዝ ሞውስ እንዲሁም የግብጹ መሃመድ አብደል አቲ በመካከላቸው ያለውን ልዩነት ለማስወገድ ቢጥሩም አልተሳካላቸውም።

እናም በሶስቱ ሚኒስትሮች ያልተሳካውን የአባይ ግድብ ውይይት እንደገና 9 አባላት ባሉበት ከሳምንት በኋላ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ግንቦት 15/2018 ለማካሄድ ቀጠሮ ይዘዋል።

በዚሁም እያንዳንዳቸው ሃገራት የውጭ ጉዳይ፣የውሃና መስኖ እንዲሁም የደህንነት ዳይሬክተሮችን በማካተት ለመወያየት ማቀዳቸው ነው የተነገረው ።

የ3ቱም ሀገራት የልዩነት መንስኤ ግብጽ ከዚህ ቀደም ከሱዳን ጋር የነበራት የውሃ ስምምነት ታሳቢ እንዲደረግ በመጠየቋ ነው።