በባህርዳር ስታዲየም ሊካሄዱ የነበሩ ጨዋታዎች ተሰረዙ

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 26/2010) የጸጥታ ስጋት በሚል ሰበብ በባህርዳር ስታዲየም ሊካሄዱ የነበሩ ጨዋታዎች ተሰረዙ፡፡

ፋይል

ሚያዝያ 26 /2010 ባህርዳር ከነማ ከኮምቦልቻ ከነማ እንዲሁም አውሥኮድ እግር ኳስ ክለብ ከሰበታ ከነማ ክለብ ጋር ዛሬ የነበረው ጨዋታ ተሰርዟል።

ውድድሩን ለመመልከት ሜዳ የገቡ ተመልካቾች ጨዋታው በመቋረጡ ከፍተኛ ቅሬታ እንዳደረባቸው የአካባቢው ምንጮች ለኢሳት ገልጸዋል።

ከፍተኛ ቁጥር ያለው የእግር ኳስ ተመልካቾች ትኬት ቆርጠው ወደ ሜዳ በመግባት ጨዋታውን በመጠባበቅ ላይ ነበሩ።

ተጫዋቾች ማሊያቸውን ለብሰው ወደ ሜዳ ለመግባት በጨረሱበት ሰዓት ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ጨዋታው ተቋርጧል።

ዳኞችም በፀጥታ ኃይሎች ማጫወት አትችሉም ተብለው በመኪና መወሰዳቸው ነው የተነገረው ፡፡

የፀጥታ ችግር በመኖሩ  ከበላይ አካል በመጣ ትዕዛዝ መሰረት ጨዋታው እንዳይካሔድ ታዟል ከመባሉ ውጭም በዝርዝር የተገለጸ ነገር የለም።

ተመልካቹ ሕዝብ አንደኛ ከሰበታና ከኮምቦልቻ ድረስ መጥተን ትኬቱን ገዝተን ከ3 ቀን በላይ ቅስቀሳ ከተደረገ በኋላ ጨዋታውን እንዲቋረጥ ማድረግ ከፍተኛ ዋጋ ያስከፍላል በማለት በምሪት ተናግረዋል ፡፡

ምንጮች እንደገለፁት ስርዓቱን የሚያወግዙና አንድነትን የሚያጎሉ መዝሙሮች ይሰሙ ነበር።

የአርበኛ በላይ ዘለቀ ቲሸርት በብዛት ይሸጥና በበርካታ ተመልካቾችም ተለብሶ እንደነበርም ታውቋል። ይህም ስጋት ሳይሆን አልቀረም ነው የተባለው ፡፡

በአሁኑ ሰዓት በርካቶች በምሪት ተቃውሟቸውን እየገለፁ ይገኛሉ ፡፡