የባህርዳር ሁለገብ ስታዲየም ሳይጠናቀቅ ርክክብ ተፈጸመ

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 26/2010) በባህርዳር የተገነባው ሁለገብ ስታዲየም ሳይጠናቀቅ የአማራ ክልል መንግስት ከሜድሮክ ኢትዮጵያ ጋር የርክክብ ስነስርአት ፈጸመ።

ፋይል

በ7 መቶ ሚሊየን ብር ተገንብቶ በ5 አመት ውስጥ ይጠናቀቃል የተባለው የባህርዳር ሁለገብ ስታዲየም የጣራና የወንበር ተከላ ሳይጠናቀቅ የአማራ ክልላዊ መንግስት ርክክብ ፈጽሟል።

በ2002 የተጀመረውና 8 አመታትን ያስቆጠረው የስታዲየሙ ግንባታ 4 መቶ ሚሊየን ብር ወጪ ከተደረገበት በኋላ በጅምር መቅረቱ ታውቋል።

ሜድሮክ ኢትዮጵያ ስታዲየሙን ባለማጠናቀቁ ከአጠቃላይ ወጭው 10 በመቶ ቅጣት ቢኖርበትም በውሉ መሰረት ግን ተፈጻሚ አልሆነም።

የባህርዳር ሁለገብ ስታዲየምን ለመገንባት የውል ስምምነት የተፈጸመው በአማራ ክልል የቀድሞው ርዕሰ መስተዳደር አቶ አያሌው ጎበዜና በሜድሮክ ኢትዮጵያ ባለቤት በሼህ መሃመድ አላሙዲን አማካኝነት ነበር።

የስቴዲየም ግንባታው ታህሳስ 2/2002 ከመጀመሩ በፊት ሼህ መሃመድ አላሙዲን ለሚያደርጉት አስተዋጽኦ ድጎማ ይሆን ዘንድ የጣና ሆቴልና አቫንቲ ተብሎ የሚታወቀው የአቶ መኮንን ገበየሁ ንብረት በሃራጅ እንዲሸጥ ተደርጎላቸው እንደነበር አይዘነጋም።

ሁለቱም ትላልቅ ሆቴሎች በርካሽ ዋጋ የተሸጠላቸው ሼህ አላሙዲን በሕዝብ መዋጮና በመንግስት ድጎማ ሊሰራ የታቀደውን ሁለገብ ስታዲየም በ5 ዓመታት ውስጥ ገንብተው ለማስረከብ ቃል ገብተው ነበር።

ስታዲየሙ 60ሺህ ተመልካቾችን የመያዝ አቅም እንደሚኖረውም በወቅቱ ተገልጾ ነበር።

ሜድሮክ ኢትዮጵያ ግንባታውን ከጀመረ ከ8 ዓመታት በላይ ቢሆነውም ስቴዲየሙ እስካሁን አልተጠናቀቀም።

በአንደኛው ምዕራፍ ወንበር ተከላና የሸራ ማንጠፍ ስራው እንደሚጠናቀቅ ቢገለጽም ይህም እንደተባለው አልተሳካም።

የወንበር ተከላው እስካሁን ያልተጀመረለት የባህርዳሩ ስቴዲየም የጣራ ንጣፍ አልተካሄደለትም።

እነዚህ ወሳኝ ስራዎች ባልተጠናቀቁበት ሁኔታ ግን የአማራ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ስታዲየሙን ባለበት ለመረከብ ተገዷል።

ሜድሮክ ኢትዮጵያ በውሉ መሰረት ስታዲየሙን ባለማጠናቀቁ 10 በመቶ ቅጣት ቢኖርበትም ክፍያውን ሳይፈጽም ውሉን አቋርጧል።

የባህርዳር ስታዲየም አለም አቀፍ ደረጃውን ጠብቆ ይጠናቀቃል ከተባለ በኋላ ለፌስቲቫልና ለብሔራዊ የበዓል ዝግጅቶች እንዲውል ተደርጎ ሲሚንቶ ላይ በመቀመጥ ውድድሮችን የመመልከቻ ቦታ ሆኗል።

የባህር ዳር ሁለገብ ስታዲየም ግንባታ መቼና እንዴት ሊጠናቀቅ ስለመሆኑ የተገለጸ ነገር የለም።