(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 26/2010) በድሬዳዋ የሶማሌ ክልሉን ፕሬዝዳንት አብዲ ዒሌን በመቃወም ሰልፍ ተደረገ።
ዛሬ ከጁማአ ስግደት በኋላ በተደረገው ተቃውሞ የአብዲ ዒሌ አስተዳደር ከስልጣን እንዲወርድ ተጠይቋል።
የሶማሌ ክልልን በሰፊው ያዳረሰው ተቃውሞ በቀጠለበት በዚህን ወቅት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሶማሌ ክልል ቅርንጫፍ ሃላፊ በአብዲ ዒሌ በተላኩ ሰዎች ተደብድበው ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው ለማወቅ ተችሏል።
አብዲ ዒሌ የገጠማቸውን ተቃውሞ ለመቀልበስ ያዘጋጁት የድጋፍ ሰልፍም እንዳልተሳካ የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
ሽንሌ ዞን የጀመረው ተቃውሞ በቅርበት በምትገኘው ድሬዳዋ ከተማ ላይ ተጽዕኖው በርትቶ ነው የሰነበተው።
በተደጋጋሚ ተቃውሞ እየተደረገባት ባለችው ድሬዳዋ ዛሬም ከጁምአ ስግደት በኋላ አብዲ ዒሌንና አመራሩን የሚያውግዙ መልዕክቶችን በማሰማት ህዝቡ አደባባይ መውጣቱን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የሶማሌ ክልሉ ተቃውሞ እምብርት በሆነችው በሽንሌ ከተማም እስከዛሬ ከነበረው ጠንከራ የተባለ ተቃውሞ እንደተካሄደም ታውቋል።
በሽንሌ ከተማ ዙሪያ ከሚገኙ የገጠር መንደሮች ሳይቀር የተሳተፉበት የሽንሌው የዛሬው ተቃውሞ የአብዲ ዒሌ አስተዳደር ከስልጣን እንዲወርድ የሚጠይቅ መልዕክት መተላለፉን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
አብዲ ዒሌ ለፍርድ ይቅረብ፣ ተሀድሶ አንፈልግም፣ የስርዓት ለውጥ ይደረግ የሚሉ መፈክሮችም መሰማታቸው ታውቋል።
ተከታታይ የህዝብ ተቃውሞ የገጠማቸው የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አብዲ ዒሌ ከፍተኛ ገንዘብ በማውጣት የማባበል ስራ መጀመራቸውን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
አዲስ የሾሟቸውን የካቢኔ አባላትን በ11ዱም የክልሉ ዞኖች በማሰማራት ተቃውሞ እንዲቆምና ወጣቶች ተደራጅተው ስራ እንዲሰሩ የሚያደርግ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚሰጣቸው ቃል በመግባት ላይ መሆናቸውን ነው ለማወቅ የተቻለው።
በቅርቡ ለተፈናቀሉት የሶማሌ ክልል ተወላጆች ከፌደራል መንግስትና ከሌሎች አካላት የተሰጠውን በሚሊየን የሚቆጠር ገንዘብ ለዚሁ የማባበያ ስራ እየተጠቀሙበት መሆኑም ተገልጿል።
የአብዲ ዒሌ አስተዳደር በአንዳንድ ቦታዎች በገንዘብ ማባበያ የድጋፍ ሰልፍ እንዲደረግ ከፍተኛ ጥረት ማድረጉን የሚገልጹት ምንጮት በተለይ በሽንሌ ዞን የተደረገው ጥረት ሙሉ በሙሉ መክሸፉን ይጠቅሳሉ።
አቶ አብዲ ዒሌ የሀገር ሽማግሌዎችን በመሰብሰብ ተቃውሞውን ከጀርባ ሆነው የሚያቀጣጥሉት ሃይሎች የክልላችንን ነዳጅ ለመዝረፍ የቋመጡ ናቸው፣ የእኛን መለያየትና መጋጨት እንደመልካም አጋጣሚ ተጠቅመው ሀብታችንን ሊዘርፉን ነው የሚል ቅስቀሳ መጀመራቸውም ታውቋል።
በሽንሌ የጀመረው ተቃውሞ ዛሬም በተለያዩ የሶማሌ ክልል አካባቢዎች የተስፋፋ መሆኑን የሚያሳዩ መረጃዎች ወጥተዋል።
ተቃውሞውን ለማስቆም የአብዲ ዒሌ ልዩ ሃይል ከአጋዚ ሰራዊት ጋር እያደረገ ያለው የአፈና ርምጃ ብዙም ውጤታማ እንዳልሆነም እየተነገረ ነው።
በሌላ በኩል በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሶማሌ ክልል ቅርንጫፍ ሃላፊ በአቶ አብዲ ዒሌ ሰዎች ክፉኛ መደብደባቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
ሃላፊው አቶ ጀማል መሀመድ ወርፋ በልዩ ሃይል ታፍነው ከተወሰዱ በኋላ ከፍተኛ ድብደባ የተፈጸመባቸው ሲሆን በእጅና እግሮቻቸው ላይ የደረሰው ጉዳት ከባድ በመሆኑ ሆስፒታል ተኝተው እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል።
ምንም እንኳን የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በህወሃት አገዛዝ የተቋቋመና በህወሃቱ ዶክተር አዲሱ ገብረእግዚአብሔር የሚመራ ቢሆንም የሶማሌ ክልሉ ተወካይ አቶ ጀማል ግን የአብዲ ዒሌ አስተዳደር የሚፈጽመውን ጭቆና በአደባባይ የሚቃወሙ እንደሆኑ ይነገርላቸዋል።
ለልዩ ሃይሉ አፈናናና ድብደባ የተዳረጉትም በዚሁ አቋማቸው እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል።