በደቡብ አፍሪካ ሰባት ኢትዮጵያውያን ተገደሉ

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 26/2010) በደቡብ አፍሪካ በ48 ሰዓታት ውስጥ ሰባት ኢትዮጵያውያን መገደላቸው ተሰማ።

ከጆሀንስበርግ በ60 ኪሎ ሜትር በምትርቀው ፓልም ሪች ወይም ቶኮዛ በሚባል አካባቢ ከትላንት ወዲያ ጀምሮ እስከዛሬ ጠዋት ድረስ 7 ኢትዮጵያውያን የተገደሉት በተደራጁ ዘራፊዎች በተወሰደ ርምጃ መሆኑ ታውቋል።

5ቱ የተገደሉት ትላንት ምሽት መሆኑን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ በቦታው ደርሶ ጉዳዩን እየተከታተለው መሆኑን አስታውቋል።

የሟቾቹ ኢትዮጵያውያንን አስክሬን ወደ ሀገር ቤት ለመላክ ዝግጅት በማድረግ ላይ መሆኑንም ገልጿል።

በደቡብ አፍሪካ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እንደዚህ ወቅት የከበደ የለም። ሀዘን ተደራርቦ እየመጣባቸው ነው።

ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ 9 ኢትዮጵያውያን በደቡብ አፍሪካ መገደላቸው በመላው ዓለም ኢትዮጵያውያንን በሀዘን አቆራምዷል።

በአክቲቪስት ገዛሀኝ ገብረመስቀል ነብሮ ግድያ ሀዘን የመታው ኢትዮጵያዊ ገዛህኝን ሸኝቶ ወደ ቤቱ ሳይገባ ሌላ ኢትዮጵያዊ ተገድሏል።

ባለፉት 48 ሰዓታት ደግሞ 7 ኢትዮጵያውያን በአንድ አካባቢ መገደላቸው ተሰማና ሀዘንኑን የከፋ አደረገው።

ለኢሳት ዜናውን ያደረሱት በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ኮሚኒት አባላት እንደገለጹት ትላንት እኩለ ሌሊት የተደራጁ ዘራፊዎች ኢትዮጵያውያን በሚገኙበት መንደር ገብተው 5ቱን ገድለው ንብረታቸውን ዘርፈው ሸሽተዋል።

ከጆሀንስበርግ በ60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ፖልም ሪጅ ወይም ቶኮዛ በሚባለው መንደር ከትላንት በስቲያ አንድ ኢትዮጵያዊ በስለት ተወግቶ የተገደለ ሲሆን በማግስቱ ትላንት ሌሊት በዚያችው መንደር አምስት ኢትዮጵያውያን መገደላቸውን ነው የደረሰን መረጃ የሚያመለክተው።

በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ሰብሳቢ አቶ ታምሩ አበበ ትላንት ሌሊት የአምስቱ ኢትዮጵያውያን ግድያ እንደተፈጸመ የድረሱልን ጥሪ ተደርጎልን ወደ አካባቢው ስናመራ ዛሬ ጠዋት አንድ ሌላ ኢትዮጵያዊ መገደሉን ሰማን ሲሉ ለኢሳት ገልጸዋል።

በድምሩ በሁለት ቀናት ውስጥ 7 ኢትዮጵያውያን ፖልም ሪጅ በተባለ መንደር መገደላቸውን ነው አቶ ታምሩ የገለጹት።

ግድያው ከዘረፋ ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ቢገመትም ጉዳዩ በምርመራ ላይ በመሆኑ የግድያውን ትክክለኛ ምክንያት አሁን ላይ መግለጽ እንደማይቻል አቶ ታምሩ ተናግረዋል።

የተገደሉት የሰባቱ ኢትዮጵያውያን ማንነት ስምና የቤተሰብ አድራሻ የታወቀ በመሆኑ ለቤተሰብ የማሳወቅ ስራ እየተከናወነ ነው ያሉት አቶ ታምሩ ነገ የሁለቱ አስክሬን ወደ ሀገር ቤት እንደሚላክም አስታውቀዋል።

በአሁኑ ጊዜ በፖልም ሪጅም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በተፈጠረው ሁኔታ ተረብሸዋል።

ያንን የማረጋጋት ስራ እየሰራን ነው ሲሉም ገልጸዋል። በየጊዜው አስክሬን መሸኘት ለእኛ ኢትዮጵያውያን አስቸጋሪና ከባድ ሆኖብናል ያሉት አቶ ታምሩ በደቡብ አፍሪካ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ዝምታ መገረማቸውን ገልጸዋል።

ኤምባሲው ጉዳዩን በተመለከተ እስካሁን የሰጠው አስተያየትም  ሆነ የወሰደው ርምጃ የለም።