በምግብ ዋስትና ፕሮግራም ስም ከተዘጋጀው ተዘዋዋሪ ብድር ከሶስት መቶ ሚሊዮን ብር በላይ መባከኑ ተጋለጠ፡፡
(ኢሳት ዜና ሚያዝያ 26 ቀን 2010 ዓ/ም)በአማራ ክልል አደጋ መከላከል ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት 312 ሚሊዮን 641 ሽህ ብር በላይ ማባከኑን የክልሉ ኦዲት ሪፖርት አጋልጧል፡፡
በክልል ደረጃ ከ2003 እስከ 2006ዓም. ከተሰራጨው ብድር ውስጥ 598 ሚሊዮን 176 ሽህ ብር ለማስመለስ እቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም፣ የተመለሰው ገንዘብ ግን 285 ሚሊዮን 562 ሽህ ብር ብቻ መሆኑን የክልሉ ኦዲተር ለክልሉ ምክር ቤት ባቀረበው ሪፖርት አመልክቷል፡፡
በእብናት ወረዳ በማህበራት በኩል ተሰራጭቶ መመለስ ከነበረበት ገንዘብ ውስጥ ከአስራ ሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ሳይመለስ መቅሬዩን ፣ በዋድላ ወረዳ ከተሰራጨው ተዘዋዋሪ ብድር ውስጥ ከ2 ሚሊዮን 491 ሽህ ብር በላይ ፤በግዳን ወረዳ ከ21 ሚሊዮን ብር በላይ አለመመለሱን ኦዲተሩ ጠቅሰዋል።
ጉድለቱን ያቀረቡት ዋና ኦዲተር ረዳት ፕሮፌሰር ገረመው ወርቁ እንደተናገሩት በስማዳ ወረዳዎች ለ312 አርሶ አደሮች አገልግሎት እንዲሰጥ ታስቦ የተገነባው መስኖ ስራ ከአንድ ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎበታል፡፡
በመስኖ ስራው የውሃ ማሳለፊያዎች ሁሉም ሙሉ በሙሉ በ’ሜታል ሽት’ ያልተዘጉ በመሆኑ በ2009 ዓም ክረምት ከካናሉ በወጣ ጎርፍ በሰባት አርሶ አደሮች መሬት ላይ ጉዳት ማድረሱ በአሰራር ላይ የተከሰተ ጉድለት መሆኑን በሪፖርታቸው አመልክተዋል።
የመስኖ ግድቡ የጎርፍ መቀልበሻ ያልተሰራለት በመሆኑ የመስኖ ቦዩ በጎርፍ ፈርሷል፡፡ይህም የሚፈሰው ውሃ በአርሶ አደሩ መሬት ላይ የአፈር መሸርሸር ጉዳት ያደረሰ መሆኑን ሪፖርቱ ይፋ አድርጓል፡፡
በራያ ቆቦ በሁለት ቀበሌዎች የካፒታል ፕሮጀክት ለመስራት ውል የወሰደው ‘ረምሃይ ጠቅላላ ውሃ ነክ ስራዎች ተቋራጭ’ ቅድሚያ 233 ሽህ 225 ብር ከተከፈለው በሁዋላ በመጥፋቱ፣ ሪፖርቱ እስኪጠናቀቅ ድረስ ሥራው አልተጀመረም።
በጉባላፍቶ ወረዳ በሴፍቲኔት ካፒታል በጀት በ2009 ዓም ለ456 አርሶ አደሮች አገልግሎት የሚውል የመስኖ ቦይ ፣ ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር በላይ ተከፍሎ ቢዘጋጅም፣ የመስኖ ግድቡ አንድ ዓመት ሳያገለግል የፈራረሰ መሆኑን በሪፖርቱ ቀርቧል፡፡
ባለፈው ዓመትም ተመሳሳይ ሪፖርት ቀርቦ የነበረ ቢሆንም የተወሰደ እርምጃ ግን የለም፡፡