በጅቡቲ ወደብ የሚገኙት የቻይናና አሜሪካ ሰራዊት እየተወዛገቡ ነው
(ኢሳት ዜና ሚያዝያ 26 ቀን 2010 ዓ/ም) በጅቡቲ ሊሞኒየር ወደብ የሚገኙ የአሜሪካ የጦር ጄቶች ከቻይና የጦር ሰፈር በሚለቀቁ ጨረሮች እየተጠቁ መሆኑን አሜሪካ ስታስታውቅ ቻይና በበኩሏ ክሱ መሰረተ ቢስ ነው ብላለች።
ፋይናንሻል ታይምስ እንደዘገበው ቻይና ባለፈው ነሃሴ ወር በጅቡቲ ወደብ የጦር ካምፕ ከመሰረተችበት ጊዜ ጀምሮ በሁለቱ ሃያላን መንግስታት መካከል የተጀመረው ውዝግብ ቀጥሎአል። ቻይና የመሰረተችው የጦር ሰፈር ከአሜሪካ በ12 ኪሜ ርቅት ላይ መገኘቱ ለአሜሪካ ሰላም የሚሰጥ አልሆነም።
አሜሪካ ከቻይና በሚለቀቅ ተደጋጋሚ ጨረር ቢያንስ አንድ አብራሪዋ ጉዳት እንደደረሰበት አስታውቃለች። ቻይና ወታደራዊ ሃይሏን በማጠናከር በአለም ላይ ያላትን ተሰሚነት ለማጎልበት እና አፍሪካንም ለመቆጣጠር በሞከረች ቁጥር ከአሜሪካ ጋር ልትጋጭ እንደምትችል አሁን የቀረበው ክስ አንዱ ማሳያ መሆኑን የፖለቲካ ተንታኞች ይገልጻሉ።
የፔንታጎን ቃል አቀባይ ዳና ሁዋይት ድርጊቱን በጣም አሳሳቢ ብለውታል። ቻይና ጉዳዩን እንድትመረምር ማሳሰባቸውንም ቃል አቀባዩዋ ተናግረዋል።
ቻይና አሜሪካ ያቀረበችው ውንጀላ መሰረተ ቢስ ነው ያለች ሲሆን፣ እንቅስቃሴዋ ሁሉ የአለማቀፍ ህግ እና የአካባቢ ህጎችን ባከበረ መልኩ እንደሚከናወን ገልጻለች።
አሜሪካ 4 ሺ የሚሆኑ ወታደሮችን ጅቡቲ በሚገኘው የጦር ካምፗ አስፍራለች። ፈረንሳይ፣ ጣሊያንና ጃፓንም በጅቡቲ የጦር ሰፈር አላቸው።