ታህሳስ 16 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አባላት ለኢሳት የአዲስ አበባ ወኪል እንደገለጡት በሰራዊቱ ውስጥ፣ የብሄር ተዋጽኦን ለመቀነስ ተብሎ እየተወሰደ ባለው እርምጃ እንዲቀነሱ የሚደረጉት በብዛት የአማራ እና የኦሮሚያ ክልል ተወላጆች ናቸው።
የመከላከያ ሚኒስትር የሆኑት አቶ ሲራጅ ፈርጌሳ የሰራዊቱን የብሄር ተዋጽኦ ለመጠበቅ መንግስት የማመጣጠን ስራ እየሰራ ነው በማለት ለፓርላማ መናገራቸው ተከትሎ፣ አባላቱ እንደገለጡት፣ የሰራዊቱን ተዋጽኦ ለማስተካካል በሚል ሽፋን አገዛዙን አይደግፉም ወይም ለአገዛዙ ታማኞች አይደሉም የተባሉ የአማራ እና የኦሮሚያ ክልል ተወላጆች በብዛት ተቀንሰዋል።
በአንድ ወታደራዊ ክፍል ውስጥ እንዲቀነሱ ከተደረጉት 20 የሰራዊቱ አባላት ውስጥ 15ቱ አማራ ሲሆኑ ቀሪዎቹ ደግሞ ከሌላ ብሄር የተውጣጡ ናቸው።
ሚኒስትር ሲራጅ ፈርጌሳ በርካታ የትግራይ ተወላጆች ከሰራዊቱ እንዲቀነሱ መደረጉን ቢናገሩም፣ የሰራዊቱ አባላት ግን የተቀነሱት ጡረታ ያለፋቸው የትግራይ ተወላጅ የመከላከያ ሰራዊት አባላት እንጅ ወጣቶች አይደለም ይላሉ።
በአማራ እና በኦሮሚያ ተወላጆች ላይ የሚታየው ደግሞ በተቃራኒው ወጣቶችን መቀነስና፣ ለመንግስት አደገኛ አይሆኑም የተባሉ በእድሜ የገፉትን የሰራዊት አባላት ማቆየት ነው በማለት አጋልጠዋል።
ወጣት የሆኑ የአማራ ና የኦሮሞ ተወላጆች እየተባረሩ በእድሜ የገፉት ብቻ እንዲቆዩ መደረጉ፣ ወጣት የትግራይ ተወላጆች የትምህርት እና የአዛዥነቱን ቦታ ለመውሰድ እንዲችሉ ታስቦ የተደረገ መሆኑን አባላቱ ይናገራሉ።
ለአለፉት 18 አመታት በሰራዊቱ ውስጥ ያገለገል አንድ መኮንን ሲናገር፣ “በርግጥም ቅነሳ አለ፣ ቅነሳው ግን ብሄርን፣ ታማኝነት፣ እውቀትንና እድሜን ግምት ውስጥ አስገብቶ የሚካሄድ ነው። የአማራ እና የኦሮሞ ተወላጅ ሆነህ፣ ታማኝ መስለህ ካልታየሀቸው፣ ከሁሉም በላይ ፊደል የቆጠርክና ወጣት ከሆነክ ፈጽሞ አትፈለግም።” ብሎአል።
በእድሜ የገፋ አማራና ኦሮሞ የትምህርት እድል ስለማይጠይቅ፣ ታዛዥ ሆኖ ይኖራል በሚል እሳቤ እንደማይቀነስ፣ የገለጠው አባሉ፣ ነገር ግን በሰራዊቱ ውስጥ ጉምጉምታ እንዳይኖር እድሜያቸው ከ65 በላይ የሆኑትን የትግራይ ተወላጆች በመቀነስ ለመሸንገል ይሞክራሉ ብሎአል።
የአማራ እና የኦሮሞ ወጣት የሰራዊቱ አባላት በሰራዊቱ ውስጥ እንዲቆዩ የሚደረገው ያልተማሩ ከሆኑ ብቻ ነው የሚለው መኮንን፣ የአልተማረ አማራና ኦሮሞ ለእግረኛ ሰራዊትነት ይፈለጋል ብሎአል።
መኮንኑ እንደሚለው በ18 አመት የመከላከያ ቆይታው በአድዋ ተወላጆችና በሌላ አካባቢ የትግራይ ተወላጆች መካከል ሰፊ የሆነ ልዩነት ይታያል።
“የአድዋ ተወላጆች ከማንም በላይ ለመንግስት ታማኝ እንደሆኑ ይናገራሉ፤ በዚህም የተነሳ የሌሎች አካባቢ የትግራይ ተወላጆች ለአድዋዎች ይሰግዳሉ፣ ልክ የሌሎች ክልሎች ተወላጆች ከአድዋ ውጭ ላሉት የትግራይ ተወላጆች እንደሚሰግዱት ሁሉ።” በማለት አክሎአል።
በመከላከያ ውስጥ እየተሰራ ያለው የመዋቅር ማሻሻያ የ አድዋ ትግራይ ተወላጆች ዘላለማቸውን አዛዥ የሌሎች ክልል ተወላጆች ደግሞ ታዛዥ ሆነው እንዲቀጥሉ የሚያድርግ ነው” ብሎአል።
ሰራዊቱ ምን ያክል ለለውጥ የተዘጋጀ ነው ተብሎ ለቀረበለት ጥያቄ ደግሞ ” የአድዋ ተወላጆች ስልጣናቸውን ላለማስነካት እስከወዲያኛው እንደሚፋለሙ ይናገራሉ፤ መድረክ በተገኘ ቁጥር የቀበርነው ነፍጠኛ አማራ ከእንግዲህ እንዲያንሰራራ አንፈቅድለትም በማለት ይናገራሉ። አዛዦች ለለውጥ ዝግጁ አይደሉም። የሌላ አካባቢ የትግራይ ተወላጆችም ቢሆኑ፣ በብዥታ ውስጥ ያሉ ነው የሚመስለው። ስሜታቸውን ማወቅ አይቻልም” ሲል መልሶል።
“የሌላ ክልል ተወላጆች አብዛኞቹ ለውጥ ፈላጊ ቢሆኑም፣ ለውጥ ስለሚመጣበት መንገድ ምንም እውቀት የላቸውም። ዘወትር እንሰለላለን ብለው ስለሚናገሩም የልባቸውን ማወቅ አይቻልም። በውሳጣቸው አንድ ነገር መቋጠራቸውን ግን በየአጋጣሚው ለመረዳት ይቻላል። የሌላ ክልል ተወላጅ የሰራዊቱ አባላት በምርጫ 97 ወቅት ትክክለኛ ስሜታቸውን አንጸባርቀዋል። ያ ሁኔታ አሁን ቢፈጠር ምናልባትም፣ ከዚያም የባሰ ነገር ሊታይ ይችላል።” ሲል አክሎ ተናግሯል።
በአለፉት 20 አመታት የአንድ ብሄር ሰራዊት የኢትዮጰያ የመከላከያ ሰራዊት ተብሎ መሰየሙን በርካታ ምሁራንና ፖለቲከኞች ሲቃወሙት ቆይተዋል።
የመከላከያ ሚኒስትሩ ወሰድነው ባሉት እርምጃ የሰራዊት ቁጥር ከህዝብ ብዛት ጋር ሲተያይ አሁንም በመከላከያ ሰራዊት ብዛት የትግራይ ተወላጆች ከፍተኛውን ስፍራ ይዘዋል።
ምንም እንኳ ሚኒስትር ሲራጅ ፈርጌሳ 100 ሺ ከሚጠጋው የመከላከያ ሰራዊት አባላት መካከል አማራ 30 ሺ343 ፣ አሮሞ 25 ሺ 205 እና ትግራይ 18 ሺ 580 ቁጥር እንዳለውና የተመጣጠነ ሰራዊት እንደተፈጠረ አድርገው ቢያቀርቡም፣ የብሄር ተዋጽኦ ከህዝብ ብዛት ጋር ከተያየ የትግራይ ተወላጆች ቁጥር አሁንም በ12 ሺ ከፍ ብሎ ይታያል።
በብሄር ተዋጽኦ ድልድሉ የአዛዥነት ቦታዎች ምን እንደሚመስሉ ሚኒስትሩ አልተናገሩም።
ግንቦት7 ከሁለት አመት በፊት ባወጣው መረጃ በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ 98 በመቶ የሚሆነው ወታደራዊ አዛዥነት ቦታዎች የተያዙት በትግራይ ተወላጆች ነው።