በጉጂ ዞን እየተካሄደ ያለው ተቃውሞ ወደ ሌሎች አካባቢዎችም ተሸጋገረ

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 25/2010) የሜድሮክ ኮንትራት መራዘሙን በመቃወም በጉጂ ዞን እየተካሄደ ያለው ተቃውሞ ወደ ሌሎች አካባቢዎችም መሸጋገሩ ተሰማ።

ከጉጂ ዞን በተጨማሪ በቦረና ዞን የወርቅ ዘረፋውን እናወግዛለን በሚል ህዝቡ አደባባይ ወጥቶ ተቃውሞውን በማሰማት ላይ መሆኑን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

በጉጂ ዞንም ተቃውሞው ለአራተኛ ቀን መቀጠሉ ታውቋል። የተራዘመውን ኮንትራት በተመለከተ በመንግስት በኩል ምላሽ ተሰቷል።

በሌላ በኩል በጅማና ሃሮማያ ዩኒቨርስቲዎች ተቃውሞ መደረጉንም ለማወቅ ተችሏል።

ካለፈው ሰኞ ጀምሮ በሁለቱ የጉጂ ዞኖች ሲካሄድ የነበረው ተቃውሞ ዛሬም በተወሰኑ አካባቢዎች መደረጉን መረጃዎች አመልክተዋል።

በሻኪሶ ትላንት በተደረገው ተቃውሞ የኮማንድ ፖስት ታጣቂዎች ከመጠን ያለፈ ሃይል በመጠቀማቸው የተጎዱ ሰዎች የህክምና ቦታዎችን አጨናንቀው መዋላቸው ተገልጿል።

ሀረቃሎ ላይ የታሰሩት ዘጠኝ የወረዳ ካቢኔ አባላት እንዳልተፈቱም ታውቋል።

የሜድሮክ የወርቅ ማዕድን ኮንትራቱ በመጋቢት 20 ካበቃ በኋላ እንዳይራዘም ከህዝብ ከፍተኛ ተቃውሞ ተደርጎ ነበር።

ሆኖም የህወሀት አገዛዝ ለተጨማሪ 10 ዓመት ኮንትራቱን አራዝሞታል።

ሰኞ ጀምሮ እየተካሄደ ያለው ተቃውሞ በአስቸኳይ ሜድሮክ አካባቢውን ለቆ እንዲወጣ የሚጠይቅ ነው።

የማዕድን ዘረፋው ይቁም፣ ከማዕድን ዘረፋው ጋር ተያይዞ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ካሳ ይከፈላቸው፣ በህዝቡ ላይ ጉዳት ያደረሱ አካላት ለህግ ይቅረቡ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በአስቸኳይ ይነሳ፣ ያለጥፋታቸው የታሰሩት ዜጎች በሙሉ ይለቀቁ የሚሉ መፈክሮችን በመያዝ ዛሬም ተቃውሞው በአንዳንድ ቦታዎች መደረጉን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

ዛሬ በአብዛኛው ተቃውሞ የተካሄደባቸው አካባቢዎች በቦረና ዞን ውስጥ የሚገኙ ናቸው።

ጉጂን የሚጎራበተው የቦረና ዞን በሜድሮክ የወርቅ ዘረፋ ላይ ተቃውሞ በማንሳት በበርካታ አካባቢዎች ሰልፍ ተደርጓል።

የዞኑ ባለስልጣናት ሁኔታውን ለማርገብ ስብሰባ የጠሩ ቢሆንም ተቃውሞ መቀጠሉን ነው ያገኘነው መረጃ የሚያመለክተው።

የኮማንድ ፖስት በሃይል ተቃውሞውን ለማስቆም ተጨማሪ ሃይል በየከተሞቹ ማስገባቱንም ለማወቅ ተችሏል።

የህዝብ ተቃውሞ በተጠናከረበት በዚህን ወቅት ምላሽ የሰጠው አገዛዙ ኮንትራቱ እንደማይሰረዝ ዋስትና መስጠት እንደማይቻል ያረጋገጠበት ነው ተብሏል።

የጤናና የአካባቢ ጥናት ተደርጎ የተሰጠ ኮንትራት በመሆኑ እየቀረበ ያለው ክስ መሰረተ ቢስ እንደሆነ የመንግስት ምላሽ ያመለክታል።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ህዝብን የሚጎዳ ኢንቨስትመንት ተቀባይነት የለውም ቢልም በፌደራል መንግስት በኩል ኮንትራቱ እንደሚቀጥል የሚግለጽ መግለጫ ነው የተሰጠው።

ከፍተኛ የጤና ጠንቅ ከማስከተል ባለፈ የአካባቢ መራቆት ያደረሰው የሜድሮክ የወርቅ ፕሮጀክት የአካባቢውን ተወላጆች ተጠቃሚ ማድረግ እንዳልቻለ ይነገራል።

ምንም አይነት ጥቅም ሳያስገኝ ህዝቡን ለከፍተኛ ጉዳት በመዳረግ ላይ ያለው የወርቅ ዘረፋ በአስቸኳይ ካልቆመ የተጀመረው ተቃውሞ እንደሚቀጥል አስተባባሪዎች በመግለጽ ላይ ናቸው።

በሌላ  በኩል በሃሮማያና በጅማ ዩኒቨርስቲ ተቃውሞ መደረጉ ታውቋል።

የታሰሩ እንዲፈቱና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ በመጠየቅ በሁለቱም ዩኒቨርስቲዎች ተቃውሞው የተደረገ ሲሆን በሻኪሶ የሚካሄደው የወርቅ ዘረፋም እንዲቆም ጠይቀዋል።