በሊቢያ ትሪፖሊ በተፈጸመ የቦምብ ጥቃት 12 ሰዎች ተገደሉ

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 24/2010) በሊቢያ ትሪፖሊ የምርጫ ኮሚሽን ዋና መስሪያ ቤት ላይ በተፈጸመ የቦምብ ጥቃት 12 ሰዎች ተገደሉ።

ጥቃቱን ፈጽመዋል ከተባሉት አሸባሪዎች አንዱ ራሱ ላይ የተጠመደውን  ቦምብ በማፈንዳት እራሱን ማጥፋቱ ታውቋል።

አብረውት የነበሩት ሌሎች ግብረ አበሮቹም ሕንጻው ላይ ተኩስ በመክፈትና ሕንጻውን በማቃጠል ተባብረውታል ብሏል ዘገባው።

ለ42 አመታት በሙሀመድ ጋዳፊ አመራር ስር የነበረችው ሊቢያ የጋዳፊን መውደቅ ተከትሎ ከ2011 ጀምሮ በቀውስ ውስጥ ትገኛለች።

ከቅርብ ግዜ አንስቶ ደሞ በተለያዩ ታጣቂ ሃይሎች ቁጥጥር ስር ናት የምትባለው ሊቢያ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት የሚፈጸምባት ቦታ ሆናለች።

ሃገሪቱ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለች ነው እንግዲህ ሃገሪቱን አስተዳድራለሁ የሚለው አካል በዚህ አመት መጨረሻ ላይ ምርጫ ለማካሄድ ያቀደውና መራጮችም መመዝገብ የጀመሩት።

ዛሬ ማለዳ ደግሞ በሀገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን ዋና መስሪያ ቤት ላይ የሽብር ጥቃት ተፈጽሞ በትንሹ 12 ሰዎች መገደላቸው ተሰምቷል።

ትሪፖሊ በሚገኘው የምርጫ ጣቢያው ዋና መስሪያ ቤት ላይ  ጥቃት ከፈጸሙት አጥፍቶ ጠፊዎች አንዱ ራሱ ለይ ያጠመደው ቦንብ በማፈንዳት ራሱን ማጥፋቱ ታውቋል።

አብረውት የነበሩት ሌሎች ታጣቂዎችም ህንጻው ላይ ተኩስ በመክፈትና በማቃጠል ተባብረውታል ብሏል ሮይተርስ በዘገባው።

የምርጫ ኮሚሽነሩ ቃል አቀባይ ካሊድ ኦማር በጥቃቱ 3 የምርጫ ኮሚሽኑ ባለስልጣናትና 4 የጥበቃ ሰራተኞች መገደላቸውን ገልጸዋል።

ኮሚሽነሩ አክለውም 2 በሰውነታቸው ላይ ቦንብ የታጠቁ ሰዎች እና እነሱን ተከትለውም ወታደራዊ ልብስ የለበሱ ታጣቂዎች ወደህንጻው ሲገቡ ማየታቸውንም ገልጸዋል።