በጉጂ ዞን የተቀሰቀሰው ተቃውሞ እንደቀጠለ ነው

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 24/2010) የሜድሮክ የወርቅ ማዕድን ኩባንያ ኮንትራት መራዘሙ ያስቆጣቸው የጉጂ ዞን ነዋሪዎች ተቃውሟቸውን ለሶስተኛ ቀን መቀጠላቸው ታወቀ ።

በሃረቃሎ ዘጠኝ የካቢኔ አባላት በኮማንድ ፖስቱ መታሰራቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

ዛሬ በበርካታ የዞኑ አካባቢዎች ተቃውሞው ተጠናክሮ በመካሄድ ላይ መሆኑም ተመልክቷል።

በተቃውሞ የሀገር ሽማግሌዎችና አባገዳዎች ሳይቀር መሳተፋቸው እየተነገረ ነው።

በአንዳንድ አካባቢዎችም የአገዛዙ ታጣቂዎች ህዝቡ ላይ ጉዳት ማድረሳቸው ታውቋል።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ማንኛውም የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ የአካባቢውን ነዋሪ መጉዳት የለበትም ሲል ቅሬታውን ገልጿል።

ካለፉት ሁለት ቀናት ይበልጥ የዛሬው ተቃውሞ ጠንካራ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።

በተለይ በሻኪሶ የዛሬው ተቃውሞ በርካታ ሰዎች የተጎዱበት መሆኑ እየተነገረ ነው።

መጋቢት 20 ኮንትራቱ ያበቃው የሜድሮክ የወርቅ ኩባንያ ለተጨማሪ 10 ዓመት እንዳይራዘም በህዝብ ዘንድ የቀረበውን ተቃውሞ ወደ ጎን በማድረግ በህወሃት የሚመራው አገዛዝ ለኩባንያው ዳግም ፍቃዱን ማደሱ የፈጠረው ተቃውሞ በጉጂ ሁለቱም ዞኖች ከፍተኛ የህዝብ ንቅናቄን አስከትሏል።

ሻኪሶ ላይ የአገዛዙ ታጣቂዎች ርምጃ በመውሰድ በህዝቡ ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን ኢሳት ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል።

በሻኪሶ ዛሬ የነበረው ተቃውሞ የአገዛዙ ሃይሎች ጭካኔ የታየበት ነው ያሉት ነዋሪዎች በርካታ ተማሪዎች መደብደባቸውና ታስረው ወደአልታወቀ ቦታ መወሰዳቸውን ገልጸዋል።

ሻኪሶ ዛሬ በአስለቃሽ ጢስ ሰማይዋ ጠቁሮ መዋሉ ነው የተገለጸ ሲሆን በጢሱ የተጎዱ በርካታ ነዋሪዎች ወደ ህክምና መውሰዳቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

በአገዛዙ ታጣቂዎች የጭካኔ ርምጃ የተቆጡ ሴቶች በከፊል ልብሳቸውን በማውለቅ በከተማዋ ዋና ዋና መንገዶች ላይ እየተዘዋወሩ ከታጣቂዎቹ ጋር ፍጥጫ ገጥመው እንደነበርም ለማወቅ ተችሏል።ታጣቂዎቹንም ከፈለጋችሁ ግደሉን ሲሉም ተደምጠዋል።

ከነገሌ ቦረና ከተማ በ30 ኪሎ ሜትር በምትርቀውና የወርቅ ዘረፋውን በመቃወም ከፍተኛ ንቅናቄ እየተደረገባት ባለችው ሀረቀሎ ከተማ ዘጠኝ የወረዳ ካቢኔ አባላት በኮማንድ ፖስቱ መታሰራቸውን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የገጠር ልማት መምሪያ ሃላፊን ጨምሮ ዘጠኙ የካቢኔ አባላት የታሰሩት ከተቃውሞ ጀርባ እጃችሁ አለበት በሚል መሆኑን የኢሳት ምንጮች መረጃ ላይ ተጠቅሷል።

የካቢኔ አባላቱ ከታሰሩ በኋላ ወደ ነገሌ ቦረና መወሰዳቸውም ተገልጿል።

የሀገር ሽማግሌዎችና አባገዳዎች ለተቃውሞ በነቂስ ከወጣው ህዝብ ጋር ወደ ሜድሮክ የወርቅ ማዕድን ጽሕፈት ቤት ድረስ በመሄድ ተቃውሟቸውን ያሰሙ መሆናቸውም ታውቋል።

የአካባቢው ባለስልጣናት ጉዳዩን እየመከርንበት ስለሆነ ምላሹን በትዕግስት እንድትጠባበቁ በማለት እንደመለሷቸው የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

በአዶላ ክብረመንግስት የመምህራን ትምህርት ኮሌጅን ጨምሮ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸው የተገለጸ ሲሆን በተማሪዎችና መምህራን ላይ ድብደባ መፈጸሙንም ኢሳት ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል።

ዛሬ ዋደራ እና ሰባ ቦሮ በተባሉ ወረዳዎች ላይም ጠንካራ ተቃውሞ መካሄዱም ታውቋል።

በዋደራ በተደረገው ተቃውሞ በሜድሮክ ኩባንያ ላይ ከቀረበው ተቃውሞ በተጨማሪ የዞኑ አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ጥላሁን ዋደራ ይነሱ የሚል ጥያቄ መነሳቱ ተሰምቷል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በአስቸኳይ እንዲነሳም ተጠይቋል።

ከፍተኛ የህዝብ ተቃውሞ ያስከተለውን የወርቅ ዘረፋ በተመለከተ የኦሮሚያ ክልል መንግስት አስተያየት የሰጠ ሲሆን የህዝብን ጉዳት የሚያስከትል ኢንቨስትመንት ተቀባይነት የለውም በማለት የክልሉ ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሃላፊ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ መናገራቸው ተገልጿል።