(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 23/2010) በአሜሪካ ከ17 አመታት በፊት በተፈጸመው የሽብር ጥቃት ሰለባ ለሆኑ ቤተሰቦች ኢራን የ6 ቢሊየን ዶላር ካሳ እንድትከፍል አንድ የአሜሪካ ፍርድ ቤት ዳኛ ትዕዛዝ ሰጡ።
የምርመራ ውጤቶች ግን ኢራን በሽብር ጥቃቱ ውስጥ የነበራትን ተሳትፎ የሚያሳይ ነገር አልተገኘም በሚል ትችት በመቅረብ ላይ ነው።
የኒዮርክ የደቡብ አውራጃ ፍርድ ቤት ዳኛ ጆርጅ ዳኒልስ ትዕዛዙን የሰጡት ትላንት መሆኑ ታውቋል።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር መስከረም 11/2000 በአሜሪካ በኒዮርክ፣በዋሽንግተንና በፔንሴልቪኒያ በተፈጸመውና ከ3 ሺ በላይ ሰው ባለቀበት የሽብር ጥቃት ከ1 ሺ ለሚበልጡት ሞት ኢራን ተጠያቂ መሆኗን ዳኛው ገልጸዋል።
የኢራን እስላማዊ መንግስት አሸባሪዎችን በማሰልጠን ተሳታፊ ነበር በሚል ዳኛው ባሳለፉት ውሳኔ የኢራን መንግስት ከ6 ቢሊየን ዶላር በላይ ለሰለባዎቹ ቤተሰቦች ካሳ እንዲከፍል ትዕዛዝ ሰተዋል።
በዳኛው ውሳኔ መሰረት ኢራን የትዳር አጋራቸውን ላጡ ለእያንዳንዳቸው 12 ሚሊየን 500 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ትክፈል ሲሉ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።
እንዲሁም ለወላጆች ለእያንዳንዳቸው 8 ሚሊየን 500 ሺ ዶላር፣ልጆቻቸውን ላጡ ለእያንዳንዳቸው በተመሳሳይ 8 ሚሊየን 500 ሺ ዶላር እንዲሁም ወንድምና እህቶቻቸውን ላጡ ደግሞ 4 ሚሊየን 250 ሺ ዶላር ኢራን እንድትከፍል ዳኛው መወሰናቸውን የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ሆኖም ይፋዊ የምርመራ ውጤቶች የኢራንን ተሳትፎ አያሳይም በሚል ውሳኔው ትችት እየቀረበበት ይገኛል።
ኢራንም በጉዳዩ ላይ የሰጠችው አስተያየት የለም።