(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 22/2010) ከቤንሻንጉል ጉምዝ አካባቢ ካማሽ ዞን የተፈናቀሉ የአማራ ተወላጆች በባህርዳር ቴክኒክና ሙያ ቅጥር ግቢ ሰፍረው እየተንገላቱ መሆናቸው ተነገረ።
ሃብት ንብረታቸው ወድሞባቸው ከቤንሻንጉል ጉምዝ የተፈናቀሉት 120 የሚደርሱ የአማራ ተወላጆች ከሰው ጋር እንዳይገናኙ ተደርገው እየተጎሳቆሉ ይገኛሉ ተብሏል።
የብአዴን አመራሮች ጉዳዩን ከመሻፈፈን ወጭ ስለተፈናቃዮች መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆናቸው ተነግሯል።
ከቤንሻንጉል ጉምዝ አካባቢ ካማሽ ዞን እንዲፈናቀሉ የተደረጉ የአማራ ተወላጆች በባህርዳር ቀበሌ 11 ዘንዘልማ መውጫ ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ ላይ ይገኛሉ።
120 ይደርሳሉ የተባሉት ተፈናቃዮች ሀብት ንብረታቸው ወድሞባቸው ከፍተኛ መጎሳቆል ደርሶባቸዋል ተብሏል ።
ከ50 ያላነሱ ወገኖች በባህርዳር ቴክኒክና ሙያ ቅጥር ግቢ ውስጥ እንዳሉ የአካባቢው ምንጮች ለኢሳት አረጋግጠዋል።
ሌሎችም በዘንዘልማ መውጫ አባይ ማዶ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን አካባቢ ባለው ስፍራ በየመንገዱ ቊጭ ብለው ታይተዋል።
ተፈናቃዮችን የአካባቢው ሕዝብ ለመርዳትና ለማነጋገር መሞከራቸውንና ቀርበው ለማናገር ሲሞክሩም በፖሊሶች መከልከላቸውን ምንጮቹ ገልጸዋል።
ዛሬ ላይ በተወሰነ መልኩ ማዋራት መቻላቸውን ተናግረዋል።
ከቤንሻንጉል ከሀብት ንብረታቸው ተፈናቅለው ባህርዳር የገቡ በግምት ከ120 በላይ ወገኖች ሰው እንዳያያቸው ተከልክሏል!
በሜዳ ላይ ሰፍረው የነበሩ ወገኖች ህዝቡ ምግብና ውሃ ይዞ ሊጠይቃቸው ሲቀርብ በስፍራው ያለው ታጣቂ ሃይል በመከልከል ህዝቡን ሲያርቁ ተስተውሏል።
ነገሩ እየበረተ ሲሄድና ሕዝቡ ቀርበን እናናግር የሚለው ጥያቄው ሲያይልም በሜዳ ላይ ሰፍረው ከነበሩት ከ100 ያላነሱትን አምጥተውበባህርዳር ቴክኒክና ሙያ ተቋም ውስጥ ከሰው እንዳይገኛኙ ራቅ አድርገው አጭቀዋቸዋል።
ለመሆኑ እንዴት መጣችሁ በምንስ ሁኔታ ትገኛላችሁ ብሎ ለመጠየቅ የሞከረው ግለሰብም በታጣቂዎች ዱላ ተደብድቦ መመለሱ ታውቋል።
በግቢው አጥር ጥግ የሚታዩት ወገኖች ለምን ከህዝቡ ጋር እንዳይገናኙ እንዳደረጓቸው የታወቀ ነገር ባይኖርም በትምህርት ቤቱ ቅዳሜና እሁድ ይሰጥ የነበረው መርሃ ግብርም እንዲሰረዝ መደረጉን ለተማሪዎቹ እንደተነገራቸው ምንጮቹ ገልጸዋል።