(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ22/2010) ሜድሮክ የወርቅ ማዕድን በሻኪሶ ስራውን እንዲቀጥል መወሰኑን ተከትሎ በአካባቢው ሕዝብ ዘንድ ተቃውሞ ተቀሰቀሰ።
በጉጂ ዞን ሻኪሶና ፊንጫ ከተማ ከጠዋት ጀምሮ ከፍተኛ የተቃውሞ ሰልፍ እየተካሄደ ነው።
ሜድሮክ ኢትዮጵያ የወርቅ ማእድን የማውጣት ስራውን እንዲያቆም ከተደረገ ከ1 ዓመት በኋላ በድጋሚ ፈቃድ በማግኘቱ የአካባቢው ህዝብ በተቃውሞ አደባባይ ወጥቷል።
ተቃዋሚዎች ከፌደራል ፖሊስ ጋር ግጭት ውስጥ ገብተው በፊንጫ እስካሁን 3 ሰዎች በአስለቃሽ ጭስ ተጎድተው ወደ ህክምና ማዕከል መወሰዳቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
ሻኪሶና አካባቢው በወርቅ ምርት የበለጸገ ምድር አለው።
ከዚህ አንጡራ ሀብት ግን የአካባቢው ህዝብ መጠቀም አልቻለም። ወርቅ ተሸክሞ በድህነት የሚማቅቅ፣ ሆስፒታል አጥቶ የሚሰቃይ፣ትምህርት ተነፍጎት ድንቁርና የተፈረደበት ህዝብ ሆኗል።
ሜድሮክ ኢትዮጵያ የተሰኘው የሼህ ሁሴን አላሙዲን የወርቅ ቁፋሮ ኩባንያ በአካባቢው ትምህርትና ጤና አስፋፋለሁ የሚል የተስፋ ቃል ሰጥቶ በአካባቢው ወርቅ ማፈስ ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል።
እንደሰጠው ተስፋ ግን ለአካባቢው ህዝብ አንዳችም የመሰረተ ልማት ሳያከናውን ቆይቷል።
የዚህ ኩባንያ ጉዳይ የኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናትን በብርቱ ሲፈታተን ቆይቷል።
በኦሮሚያ ክልል የተከሰተውን የህዝ ንቅናቄን ተከትሎ የሻኪሶና አካባቢዋ ህዝብም በሜድሮክ የወርቅ ኩባንያ ላይ ተቃውሞውን አጠናክሮ ቀጥሏል።
ከዚህ ቀደም የሚደረገውን ተቃውሞ በአጋዚና በፌደራል ፖሊስ የሃይል ርምጃ ሲያፍን የዘለቀው የህወሃት አገዛዝ በመላው ኦሮሚያ ህዝባዊ አመጽ ሲቀጣጠል የሻኪሶን ህዝብ ተቃውሞ መግፋት ከማይችልበት ጊዜ ላይ ደረሰ።
ይህን ተከትሎም ለ10 ዓመት ኮንትራት የወሰደው የሜድሮክ የወርቅ ኩባንያ ለተጨማሪ 10 ዓመት እንዳይራዘምለት ተደረገ።
ግን ብዙም አልቆየም። የህዝብ ንቅናቄ ጋብ ማለቱን ተከትሎ ከሰሞኑ የሜድሮክ የወርቅ ኩባንያ የጠየቀውና ለተጨማሪ 10 ዓመታት ወርቅ እያፈሰ እንዲወስድ የሚፈቅድለት ኮንትራት መሰጠቱ ተገለጸ።
ይህም ቆሞ የነበረውን የህዝብ ተቃውሞ ዳግም እንዲቀሰቀስ አደረገው።
ለኢሳት የደረሰው መረጃ እንዳመለከተው የሜድሮክ ኩባንያ ኮንትራቱ መራዘሙ የሻኪሶንና አካባቢውን ህዝብ አስቆጥቷል።
ዛሬ ሻኪሶን ጨምሮ በ5 ከተሞች ከፍተኛ የተቃውሞ ሰልፍ ተካሂዷል።
በፊንጫም እንዲሁ ህዝብ አደባባይ በመውጣት የወርቅ ዘረፋውን አጥብቆ እንደሚያወግዝ ገልጿል።
ተቃውሞ ከሻኪሶ ሌላ በ4 ከተሞች የተካሄደ ሲሆን በብዙ ሺህ የሚቆጠር ህዝብ ቁጣውን በመግለጽ ሜድሮክ በአስቸኳይ አካባቢውን ለቆ እንዲወጣ ጠይቋል።
በፊንጫው ተቃውሞ የአገዛዙ ታጣቂዎች አስለቃሽ ጢስ በመተኮስ 3 ሰዎችን መጉዳቱንም ለማወቅ ተችሏል።
ነገ ተቃውሞው በሌሎች በርካታ ከተሞች ሊካሄድ እንደሚችል ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በሌላ በኩል በዲላ ዩኒቨርሲቲ የሚማርሩ የኦሮሞ ተወላጆች በዛሬው ዕለት የተቃውሞ ሰልፍ አድርገዋል።
በባለፈው ህዝባዊ ንቅናቄ ወቅት የታሰሩ የዩኒቨርስቲው ተማሪዎች ባለተፈቱበት ሁኔታ መማር አንችልም በማለት ያሰሙትን ተቃውሞ ሌሎች የዩኒቨርስቲው ተማሪዎችም መሳተፋቸውን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።