(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 19/2010)ሰሜንና ደቡብ ኮሪያ በመካከላቸው ያለው ጦርነት ማክተሙን አወጁ።
ከ63 አመታት በኋላም የሰሜን ኮሪያው ፕሬዝዳንት ኪም ጆንግ ኡን የደቡብ ኮሪያን ድንበር ተሻግረው ከአቻቸው ሙን ጄ ኢን ጋር መገናኘታቸው ተሰምቷል።
ሁለቱ መሪዎች በሰላጤው የነበረው ጦርነት ማክተሙን እውን ለማድረግም ለሰላም፣ለብልጽግናና ለአንድነት በጋራ ሊሰሩ የፓንሙንጆም ስምምነትን ተፈራርመዋል።
ሰሜን ኮሪያና ደቡብ ኮሪያ በሰጣ ገባና በጠላትነት ሲፈላለጉ 63 አመታትን አስቆጥረዋል።
በየጊዜው በድንበሮቻቸው አካባቢ በሚቀሰቀሱ ግጭቶች የሰላጤው አካባቢ ሰላም ርቆት ቆይቷል።
ዛሬ ላይ ግን ለዘመናት በግጭትና በትንኮሳ ይናጥ የነበረው አካባቢ የሰላም አየር እንዲነፍስበት ሆኗል።
ሁለቱ ኮሪያዎች ለዘመናት ላይነኩት አጥረውት የነበረውን ድንበር ዛሬ ላይ የሰሜን ኮሪያው ፕሬዝዳንት ኪም ጆንግ ኡን ተሻግረውት ገብተዋል።
የደቡብ ኮሪያው አቻቸው ሙን ጄ ኢንም እጃቸውን ዘርግተው ተቀብለዋቸዋል።
ኪም ጆንግ ኡን በ63 አመታት ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ደቡብ ኮሪያን የጎበኙ የሃገራቸው መሪም ሆነው ስማቸውን አስመዝግበዋል።
የሁለቱ መሪዎች የመጀመሪያ የድንበር ላይ ሰላምታንም በካሜራ መስኮታቸው ላይ አስቀርተውታል።
የሰሜን ኮሪያው መሪ ታሪካዊ ነው የተባለውን የጸብ ግድግዳ ተሻግረውት ገብተዋል ሲሉም መገናኛ ብዙሃኑ የሰላሙን ዜና ለአለም አውጀዋል።
ታሪካዊ ነው በተባለው በዚህ የኪም ጆንግ ኡን ጉብኘትም በሁለቱ ኮሪያዎች መካከል ለ63 አመታት የቆየውን ቁርሾ ወደ ጎን በማለት ለሰላም ለፍቅርና ለአንድነት እንሰራለን ሲሉ በአካባቢው የተሰየመውን የፓንሙንጆምን ስምምነትን ተፈራርመዋል።
አካባቢውን ከኒዩክለር ነጻ ቀጠና ለማድረግም ከስምምነት ላይ ደርሰዋል ብሏል ቢቢሲ በዘገባው።
ኪም ጆንግ ኡን መጪው ግዜ የሰላም ግዜ ነው ሲሉም ተደምጠዋል።
ኡን ከዚህ በኋላ የኮሪያ ሰላጤ የሰላም ዘመን ይሆንለታል ሲሉም አክለዋል።
የደቡብ ኮሪያው ሙን በበኩላቸው የአለም ሁሉ አይን የኮሪያ ሰላጤ ላይ በመሆኑ የተሸከምነው ሃላፊነት ቀላል አይደለም ብለዋል።
ከሁለቱ ኮሪያዎች መለያየት በኋላ ሰሜን ኮሪያን ሲመሩ ሶስተኛ ሰው የሆኑት ኪም ጆንግ ኡን የኒዩክለር ስምምነትን በተመለከተ ከደቡብ ኮሪያ መሪ ጋር ስምምነት ለማድረግ ተነሳሽነት ያሳዩ የመጀመሪያው መሪ ናቸው ሲሉ መገናኛ ብዙሃኑ ዘግበውታል።
የደቡብ ኮሪያው መሪ ሙን የሰሜን ኮሪያውን መሪ ኪም ጆንግ ኡን ወደ ሃገራቸው ለመምጣት የደረሱበትን ውሳኔ ጠንካራ ነው ሲሉ አሞግሰውታል።
የአለምን ትኩረት ስቦ የሚገኘው የሁለቱ አቻዎች ግንኙነት ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ትራምፕም የሚያኮራ ተግባር የሚል ሙገሳ ተችሮታል።