(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ19/2010) ባለፈው ቅዳሜ በጆሀንስበርግ ለተገደለው አክቲቪስት ገዛህኝ ገብረመስቀል ነብሮ የስንብት ፕሮግራም ተካሄደ።
የቀብር ስነስርዓቱ ነገ እንደሚፈጸም የደረሰን መረጃ ያመልክታል።
የአክቲቪስት ገዛህኝ ወላጅ እናት ትላንት ምሽት ከአዲስ አበባ ደቡብ አፍሪካ መግባታቸውም ታውቋል።
በሌላ በኩል የዋሽንግተን ዲሲ የኢትዮጵያውያን ግብረሃይል ዛሬ በደቡብ አፍሪካ ኤምባሲ ደጃፍ የሻማ ማብራት ስነስርዓት የሚያደርግ መሆኑን አስታውቋል።
የዋሽንግተን ዲሲ የኢትዮጵያውያን ግብረሃይል በአክቲቪስት ገዛህኝ ነብሮ የቀብር ስነስርዓት ላይ የሚገኝ አንድ አባሉን ወደ ደቡብ አፍሪካ መላኩንም አስታዉቋል።
ያለፈው ቅዳሜ በአንድ ደቡብ አፍሪካዊ ነፍሰ ገዳይ ህይወቱን ያጣው አክቲቪስት ገዛህኝ ገብረመስቀል ወላጅ እናት ትላንት ምሽት ላይ ደቡብ አፍሪካ ገብተዋል።
ወዳጆቹ፣ ጓደኞቹ፣ ቤተሰቦቹና በደቡብ አፍሪካ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን በአውሮፕላን ማረፊያ በመገኘት ለገዛህኝ እናት አቀባበል አድርገውላቸዋል።
በጆሃንስበርግ በሚገኘውና የገዛህኝ ቤተሰቦች ለቅሶ በተቀመጡበት የቅድስት ስላሴ ቤተክርስቲያን ሲደርሱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ለቀስተኞች በሀዘን የተቀበሏቸው መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።
በወጣው መርሃ ግብር መሰረት የአክቲቪስት ገዛህኝ ገብረመስቀል ነብሮ የቀብር ስነስርዓት በነገው ዕለት ይፈጸማል።
ዛሬ የመጀመሪያው የስንብት ወይም የመታሰቢያ ፕሮግራም መካሄዱንም የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
በጆሀንስበርግ አርኪዲዎስ ካቴድራል ቤተክርስቲያን አዳራሽ በተከናወነው የመታሰቢያና ስንብት ፕሮግራም በደብቡ አፍሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በመገኘት አሸኛኘት አድርገዋል።
አክቲቪስት ገዛህኝ በህይወት ዘመኑ እንደልጅ ለእናቱ፣ እንደ ባል ለሚስቱ፣ እንደአባት ለልጆቹ፣ እንደኢትዮጵያዊ የነጻነት ታጋይ ለወገኖቹና ለሀገሩ ያደርጋቸው ተግባራት በሰፊው ተነስተው በፕሮግራሙ ተስተጋብተዋል።
በፕሮጋራሙ ላይ የጆሀንስበርግ ፖሊስ አመራሮች ተገኝተው ገዘህኝ ለከተማዋ ጸጥታና ደህንነት ያደረገውን አስተዋጽኦ በመግለጽ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
የስንብት ፕሮግራሙ ነገ ከቀብር ስነስርዓቱ ቀደም ብሎ ግድያ በተፈጸመበትና አክቲቪስት ገዛህኝ በሚሰራበት የሀበሻ የንግድ ሱቆች አካባቢ እንደሚከናወን ከወጣው መርሀግብር ለመረዳት ተችሏል።
ነገ ዕለት ከሚከናወነው የሽኝት ፕሮግራም በኋላ በዚያው የቀብር ስነስርዓቱ ወደ ሚፈጸምበት ዌስት ፓርክ መካነ መቃብር በማምራት የመጨረሻው ግብዐተ መሬቱ እንደሚፈጸም ነው ከመረሀ ግብሩ ማወቅ የተቻለው።
በሌላ በኩል በመላው ዓለም ኢትዮጵያውያን ለአክቲቭስት ገዛህኝ ነብሮ የሻማ ማብራትና የጸሎት ፕሮግራም በማካሄድ ላይ ይገኛሉ።
ዛሬ በዋሽንግተን ዲሲ ደቡብ አፍሪካ ኤምባሲ በኢትዮጵያውያን የተዘጋጀ የሻማ ማብራት ስነስርዓት እንደሚካሄድ ታውቋል።
በዋሽንግተን ዲሲ የኢትዮጵያውያን ግብረሃይል የተዘጋጀው ይህው ፕሮግራም የአክቲቪስት ገዛህኝ ህልምን ከዳር ለማድረስ ቃል እንገባለን በሚል እንደሚከናወን ያገኘነው መረጃ ያመልክታል።
ግብረሃይሉ ለደቡብ አፍሪካ ኤምባሲ ደብዳቤ የሚያስገባ ሲሆን ደብዳቤው የደቡብ አፍሪካ መንግስት የአክቲቪስት ገዛህኝ ነብሮን ግድያ ትኩረት ሰጥቶ እንዲመረምረው የሚጠይቅ ነው ተብሏል።
በቀብር ስነስርዓቱ ላይም የሚገኝ አንድ አባሉን መላኩን ያስታወቀው ግብረሃይሉ የአክቲቪስት ገዛህኝን ቤተሰብ ለመደገፍና የግድያውን ምርመራ ለማከናወን የሚረዳ ገንዘብ በማሰባሰብ ረገድ የበኩል ድርሻ እንደሚወጣ አስታውቋል።