መዲናዋ በዳቦ ፈላጊዎች ወረፋ መጨናነቋ ተሰማ

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 19/2010) መዲናዋ አዲስ አበባ በዳቦ ፈላጊዎች ወረፋ መጨናነቋ ተሰማ።

በከተማዋ የዳቦ ዋጋ ከሚገባው በላይ መናሩንና አንድ ብር ይሸጥ የነበረው የዳቦ ዋጋም አንድ ብር ከ75 ሳንቲም መግባቱ ታውቋል።

የከተማዋ መስተዳደር ችግሩ የተከሰተው በውጭ ምንዛሪ እጦት  ምክንያት መሆኑን  አስታውቋል።

ላለፉት አመታት ተባብሶ የቀጠለውና ስር የሰደደው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ወደ ሃገር ውስጥ ተገዝቶ የሚገባውን ስንዴ በመቀነሱ የአዲስ አበባ ዳቦ ቤቶች በወረፋ መጨናነቃቸውን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

በኮልፌ ቀራንዮ፣ልደታ፣ፒያሳ፣አራት ኪሎና መገናኛ ተዟዙረው የተመለከቱት ምንጮቻችን ከተከሰተው የዳቦ እጥረት በተጨማሪ አንድ ብር ሲሸጥ የነበረው ዳቦ 1 ብር ከ75 ሳንቲም እየተሸጠ መሆኑንም ገልጸዋል።

በዳቦ እጥረትና ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ላይ የዳቦ ቤት ባለቤቶችን ያነጋገሩት ምንጮቻችን የስንዴ ዱቄት በኮታ የሚሰጣቸው ከመሆኑ ባሻገር ከተመደበላቸው ኮታም የደረሳቸው ግማሽ ያህሉ እንደሆነ ተናግረዋል።

በዚህ ከቀጠለም ንግዳቸውን እስከመዝጋት ሊሄዱ እንደሚችሉ አሳስበዋል።

አንዳንድ የከተማዋ ነዋሪዎች በበኩላቸው በተከሰተው የዳቦ እጥረትና ውድነት ምክንያት ልጆቻቸው ያለምንም ምግብ ጦማቸውን ወደ ትምህርት ቤት ለመሄድ መገደዳቸውን ተናግረዋል።

በዚህም ምክንያት ለትምህርታቸው ትኩረት መስጠት እንደተሳናቸው በምሬት ገልጸዋል።

የንግድ ሚኒስቴር የችግሩ መንስኤ ምን እንደሆነ የሕወሃት የግል ንብረት በሆነው ሬዲዮ ፋና ተጠይቆ ከውጭ ምንዛሪ እጥረት ጋር የተያያዘ መሆኑን አስታውቋል።

በተያዘው አመት 200ሺ ሜትሪክ ቶን ስንዴ ከውጪ በግዥ ለማስገባት የታቀደ ቢሆንም የውጭ ምንዛሪ ባለመኖሩ ግዥው መጓተቱን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ገልጿል።

ላለፉት 27 አመታት የግብርና መርህ ፖሊሲን እንደ ዋና ፖሊሲ የሚወስደው የሕወሃት አገዛዝ ስኳር፣ዘይትና ስንዴን የመሳሰሉ የግብርና ምርቶችን ከውጭ ማስገባቱ የፖሊሲው ውጤታማ አለመሆንን እንደሚያሳይ ሙያተኞች መግለጻቸው የሚታወስ ነው።