የዳባት ከተማ ነዋሪዎች የወልቃይት ጉዳይ የኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄ ጭምር ነው አሉ
(ኢሳት ዜና ሚያዝያ 18 ቀን 2010 ዓ/ም) “የከተማዋ ነዋሪዎች እንደሚሉት የአማራ ድንበር ተከዜ ነው። የድንበሩ ጉዳይ ፖለቲካዊ ውሳኔ ሊሰጠው ይገባል” ብለዋል።
የዳባት ህዝብ ከመንግስት አንዳች ጥቅም አግኝቶ አያውቅም፡፡ለሃያ ሰባት ዓመታት ያለአንዳች እገዛ ህብረተሰቡ እርስ በእርሱ እየተረዳዳና በአካባው ካሉ ህዝቦች ጋር እየተሸማገለ የሚኖር እንጅ በገዥው መንግስት ፍትህ አግኝቶ እንደማያውቅ ነዋሪዎች ይናገራሉ።
የዳባት ህዝብ አስጠግቶ ያበላቸውና ያጠጣቸው ጎረቤቶች በህዝቡ ላይ ቁርሾ በመያዝ በከተማዋ እድገት ላይ ከፍተኛ ጫና በማድረግ ወደ ኋላ እንደጎተቷት የሚናገሩት ተቆርቋሪ ፣ መድረክ ሰላገኘን እንናገራለን በማለት “በአጎረስኩ እጄን ተነከስኩ” የሚለው ተረት በከተማዋ ህዝብ ላይ ደርሷል ብለዋል።
የዳባት ህዝብ የሞተው ልማቱ ከተነጠቀ በኋላ መሆኑን የተነገሩት ቅሬታ አቅራቢ “ቦታችን ተቀምተናል፣ልማታችንና መሬታችን ተቀምተናል ” በማለት ወልቃይትን የተነጠቁት በሟቹ ጠቅላይ ሚኒስቴር ተንኮል መሆኑን በቁጭት ተናግረዋል፡፡
“እኛ የሞትነው ወልቃይትን ጠገዴ ከተነጠቅን በኋላ ነው፡፡ ሞታችን ሞት የሆነው፣ ተቀብረን ላንድን የሞትን ነን፡፡የዛሬው ችግር እርሱ የጣለብን ቁረሾ ነው!” በማለት ምሬታቸውን ሲገልጹ ይሰማሉ፡፡
በተያያዘ ዜና ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር አብይ አህመድ ከጎንደር ከተማ ህዝብ ጋር ባደረጉት ውይይት አንድ የጎንደር ከተማ ነዋሪ የአማራ ክልልን ወሰን በተመለከተየተናገሩት በበርካታ የክልሉ ህዝብ ተደግፎ በባህርዳርም በድጋሚ የተጠየቀ ጥያቄ ነው፡፡
“የአማራ ድንበር ተከዜ ነው” የሚሉት የከተማዋ ነዋሪ የድንበሩ ሁኔታ ‘ፖለቲካዊ ውሳኔ’ እንደሚያስፈልገው ያሳስባሉ፡፡በደርግ ሰዓት ‘ተሰኔ’ የኢትዮጵያ አካል እንደነበረች ያወሱት ተናጋሪ ፣ከደርግ ሽንፈት በኋላ ኤርትራ እንደጠቀለለቻት አስታውሰዋል፡፡ከቅርብ ጊዜ ትዝታቸው ጨልፈው የተናገሩት የጎንደር ከተማ ነዋሪ ‘አሰብ’ም ለጣሊያኖች በግመልና በመሳሪያ ከተሰጠ በኋላ ፣ዛሬ በኤርትራ ስር በመሆኑ ሃገሪቱ ችግር ላይ እንድትወድቅ አድርጓል፡፡ በመሆኑም ከአማራ ክልል የተወሰዱት መሬቶች ነገ በሚከሰተው የመገንጠል ጥያቄ የሃገሪቱን ጥቅም ሊያሳጣ ስለሚችል በፊት የነበረው የአማራ ክልል በሁሉም አቅጣጫ ሊከበር እንደሚገባ አብራርተዋል፡፡
ሌላው የእድሜ ባለጸጋ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲያሳስቡ ፤ “ሊሆን የሚገባውን መልዕክት ላስተላልፍ” ካሉ በኋላ የወልቃይት ጉዳይ ጥያቄው የወልቃይቶች ጥያቄ ብቻ ሳይሆን ጥያቄው የኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄ በተለይ የአማራው ህዝብ ጥያቄ መሆኑን በመናገር ውሳኔ ይሰጠው ዘንድ ጠይቀዋል፡፡