ሰራተኞች ደቡብ ሱዳን ውስጥ የደረሱበት ጠፋ

 

ፋይል

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 18/2010) በሰብአዊ እርዳታ ላይ የተሰማሩ 10 ሰራተኞች ደቡብ ሱዳን ውስጥ የደረሱበት ጠፋ።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንዳስታወቀው እነዚህ በሰብአዊ አድራጎት ስራ ላይ የተሰማሩት ግለሰቦች የተሰወሩት ትላንት ረቡዕ መሆኑ ታውቋል።

ሁሉም የደቡብ ሱዳን ዜጎች መሆናቸውም ተመልክቷል።

በተባበሩት መንግስታት የደቡብ ሱዳን የሰብአዊ እርዳታ ጉዳዮች አስተባባሪ አለይን ኖውዴሁ ለመገናኛ ብዙሃን እንደገለጹት የተባበሩት መንግስታትና ሌሎች የእርዳታ ድርጅት ሰራተኞችን የጫኑ ተሽከርካሪዎች ዪ ከተባለው ማዕከላዊ የደቡብ ሱዳን ከተማ ቶር ወደ ተባለው ከተማ ረቡዕ ማለዳ በመጓዝ ላይ ነበሩ።

በጉዞ ላይ እያሉ ድንገት የተሰወሩትና የደረሱበት ያልታወቀው የእነዚህ የእርዳታ ሰራተኞች ጉዳይ እጅጉን አሳሳቢ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት አስተባባሪው ገልጸዋል።

ሮይተርስ ከጁባ ደቡብ ሱዳን እንዳስታወቀው  ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ የተሰወሩትን ሰዎች በተመለከተ ምንም የተገኘ ፍንጭ የለም።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2013 በፕሬዝዳንት ሳልቫኬርና በቀድሞው ምክትል ፕሬዝዳንት ሬክ ማቻር መካከል የተፈጠረውን ውዝግብ ተከትሎ በተቀሰቀሰው  የእርስ በርስ ጦርነት ሃገሪቱ በከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ትገኛለች።

በግጭቱ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲገደሉ ከሟቾቹ ውስጥ አንድ መቶ የሚሆኑት የእርዳታ ሰራተኞች ናቸው።

አለም አቀፉ ቀይ መስቀል ሊር በተባለው የደቡብ ሱዳን ከተማ በሚገኘው ማዕከሉ ላይ የተሰነዘረበትን ጥቃት ተከትሎ ከ15 ቀናት በፊት የእርዳታ ስራውን አቋርጦ ሰራተኞቹንም ወደ ርዕሰ ከተማዋ ጁባ አዛውሯል።

ለመንግስት ትሰልላላችሁ በሚል ታግተው ተወስደው የነበሩ 7 የእርዳታ ሰራተኞች ለሶስት ሳምንታት ያህል በታጣቂዎች እጅ ቆይተው ከ2 ሳምንት በፊት ተለቀዋል።